ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኢፈርት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አባዲ ዘሙ ከሀላፊነታቸው ተነስተው በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ሐይሌ ኪሮስ ገሰሰ የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ሀላፊነታቸውን እንዲለቁ ተደርገዋል።
አቶ ሀይለ ኪሮስ ገሰሰ ከቻይና አምባሳደርነት ሲነሱ የቀድሞውን የዶ/ር ተቀዳ አለሙን የምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒሰትርነት ቦታ እይዛለሁ ብለው ገምተው የነበረ ቢሆንም፣ ቦታው ለአቶ ብርሀነ ገብረክርስቶስ እንዲሰጥ ተደርጓል።
አቶ ሀይለ ኪሮስ በሱዳን አምባሳደር ተደርገው መሾማቸው ሲያበሳጫቸው መቆዬቱን እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቁዋቸው ሰው ለኢሳት ገልጠዋል።
ከሁሉም በላይ ወ/ሮ አዜብ በህወሀት ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ጉልበታቸውን የሚቃወሙት አቶ ሀይለ ኪሮስ ፣ ወ/ሮ አዜብ ሱዳን በሚመላለሱበት ጊዜም ተገቢውን ክብር እንደማይሰጡዋቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አቶ ሀይለ ኪሮስ የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ እንዲነሱ መደረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በሁዋላ በህወሀት አመራር ውስጥ ሀላፊነት ይዘው ለመቆዬት ፍላጎት እንደሌላቸውና በጡረታ ለመገለል መፈለጋቸው ታውቋል።
በእርሳቸው እግር እንዲተኩ የተደረጉት የህወሀት የስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩትና አቦይ ስብሀትን ተክተው የህወሀትን የንግድ ኩባንያ በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት አቶ አባዲ ዘሙ ሲሆኑ፣ አቶ አባዲ ዘሙም ከዘወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።
በውጭ ጉዳይ አሰራር ታሪክ ውስጥ የሱዳን አምባሳደር ሆኖ መሾም እንደ ቅጣት እንደሚቆጠር የሚናገሩት ውስጥ አዋቂዎች፣ አቶ አሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ከቆዩ በሁዋላ በሰሩት ጥፋት የሱዳን አምባሳደር ሆነው እንዲሾሙ መደረጉን አይዘነጋም።
ነባሩ የህወሀት ታጋይ አባዲ ዘሙም፣ ከኢፈርት ስራ አስኪያጅነት ወርደው የሱዳን አምባሳደር እንዲሆኑ ሲደረግ ፣ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ለፈጠሩት አለመግባባት ቅጣት ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን በርካታ የስልጣን ቦታዎችን እየተቆጣጠሩ መምጣታቸው ፣ በህወሀት ካድሬዎች ውስጥ ክፍፍል ሊያስነሳ እንደሚችልም ፍንጮች መታዬት መጀመራቸውን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ህወሀት በአቶ አባዲ ዘሙ ቦታ አዲስ ስራ አስኪያጅ ይሹም ወይም ወ/ሮ አዜብ የአዛዥነቱን ቦታ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠሩ የታወቀ ነገር የለም።