የህወሃት ባለስልጣናት ከኦብነግ ጋር አደገኛ ድርድር እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ
(ኢሳት ዜና የካቲት 9 ቀን 2010ዓ/ም) በኢትዮጵያ ሶማሊ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ የሚከታተለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ አብዱላሂ ሁሴን እንደገለጸው በናይሮቢ የሚደረገው ድርድር ከዚህ ቀደም ይደረጉ ከነበሩት ድርድሮች በይዘቱ የተለዬ ነው። ህወሃቶች ሞቃዲሾ ያሉ የሶማሊ መንግስት ባለስልጣናትንና በገንዘብ የገዙዋቸውን ሽማግሌዎች ናይሮቢ ጋብዘው ማምጣታቸውንና እነዚህ ሰዎች በኦብነግ ላይ ተጽዕኖ ፈጥረው ከሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲሌ ጋር አብረው እንዲሰሩ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ህወሃት፣ “እኛ ከስህተታችን ተምረናል። ይቅርታ ይደረግልን፣ ከአሁን በሁዋላ ከእናንተ ጋር ነው የምንሰራው፣ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ትችላለች፣ ስልጣኑን ወይ ኦሮሞ ወይ አማራ ነው የሚይዘውና ለእናንተ ከእኛ ጋር ማበራችሁ ይጠቅማል” በማለት ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን አቶ አብዱላሂ ተናግሯል።
የሶማሊ ክልል ህዝብ በተለይም የኦጋዴን ተወላጆች አካሄዱን በፍጹም እንዳልተቀበሉትና “ብንሞትም ብንተርፍም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንጅ፣ ህጻን ልጆቻችንን በሄሌኮፕተር እየጫኑ ከሚሸጡት ሰዎች አይደለም” በማለት ተቃውሞ እያሰሙ መሆኑን አቶ አብዱላሂ ገልጿል።