የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ስልጣን መልቀቅ መሰረታዊ ጥያቄውን አይመልሰውም ሲሉ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ

የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ስልጣን መልቀቅ መሰረታዊ ጥያቄውን አይመልሰውም ሲሉ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ
(ኢሳት ዜና የካቲት 9 ቀን 2010ዓ/ም) ኢሳት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደገለጹት የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅ ህዝቡ የሚያነሳውን ዋናውን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም፡
የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ሊ/መንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ ፣ ውሳኔው በኦሮምያ ያለውን ውጥረት ለማስተንፈስ ተብሎ የተደረገ ነው ብለው እንደሚያስቡና ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሮ ትርጉም ያለው የሽግግር ጊዜ እስካልተመሰረተ ድረስ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
ኢህአዴግ ታዋቂ የሆኑ እስረኞችን በመፍታት ትግሉን ለማቀዝቀዝ ያደረገው ሙከራ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ግርማ አሁንም በሺ የሚቆጠሩ ያልተዘመረላቸው ጀግኖች በእስር ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙና እነዚህን በመፍታት ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ተነጋግረው የሽግግር መንግስት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሲያመቻቹ ብቻ ለውጡ እውን እንደሚሆን አቶ ግርማ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኦህአዴድ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ቢይዝ የተሻለ ነው በሚል የአንዳንድ ባለስልጣናት ስምም እየተጠቀሰ ጠ/ሚኒስትር እንዲሆኑበማህበራዊ ሚዲያዎች ሃሳቦች እየቀረቡ ነውና ይህ ለጥያቄው መሰረታዊ መልስ ይሰጣል ብለው ያስባሉ ወይ ለተባሉት አቶ ግርማ፣ አቶ ለማ ወይም አንድ የተሻለ ሰው ቢመጣ ለሚጠየቀው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተሻለ እድል ሊኖር ይችላል ብለዋል።
ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩላቸው፣ አቶ ሃይለማርያም ቅድሞውንም ስልጣን የሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው፣ የእርሳቸው ከስልጣን መውረድ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የሽግግር ሂደቱን ለማስጀመር እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ቢመጡ መልካም ነው የሚሉ ሰዎች ቢኖርም፣ አቶ ለማም ሆኖ ከተቃዋሚዎች አንዱ ቢሾሙ፣ አሁን ባለው ስርዓት ምንም ለውጥ እንደማያመጡ ገልጸዋል። ወሳኙ በፍጥነት ሁሉንም ሃይሎች ያካተተ የሽግግር ጊዜ መንግስት መመስረት መሆኑንና ይህንንም በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል
በሌላ በኩል የአሜሪካ ኢምባሲ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ሰራተኞቹ ከአዲስ አበባ ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል። ኢምባሲው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ ተለዋዋጭና በማንኛውም ጊዜ ወደ አስከፊ ሁኔታ ሊለወጥ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።