(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 21/2011) በህክምና ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸሙ የስራ ቦታ የመብት ጥሰቶችን ጨምሮ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲከበር በመጠየቅ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተቃውሞ ተደረገ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን የተነሱትን ጥያቄዎች ለመፍታት እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ፣ በአርሲ አሰላ፣ በጂማና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በህክምና ባለሙያዎች እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ የደምወዝ ጭማሪ፣ የስራ ሰዓት ገደብና ስራ ደህንነት ዋስትና በመንግስት በኩል እንዲሰጥ ተጠይቋል።
ዶክተር አሚር በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የባለድርሻ አካላት ተከታታይ መድረክ ይዘጋጃል ብለዋል።
ተቃውሞው የተጀመረው ቀደም ብሎ ቢሆንም ላለፉት ሁለት ሳምንታት ግን በተደራጀና በተጠናከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ተቃውሞው ክልልና ቋንቋ አልገደበውም።
በየቦታው በመካሄድ ላይ ያለው የህክምና ባለሙያዎች ጥያቄ ሙያው ተገቢውን ቦታና ክብር ባለማግኘቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀና የሙያውንም ደረጃ እያበላሸው እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሁለት የጂማ የህክምና ማዕከል ተለማማጅ ዶክተሮች ላይ ለህይወት አስጊ የሆነ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የማዕከሉ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ በማድረግ መንግስት የስራ ደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የህክምና ሰራተኞች አጠቃላይ የመብት ጉዳዮችንም በማንሳት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ በኋላ ጉዳዩ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ዘንድ እንዲነሳ አድርጎታል።
በተለይም በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዕጩ ተማሪዎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተው ለተቃውሞ በወጡ ጊዜ የተወሰደባቸው ርምጃ ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸውን አስቆጥቷል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ጥያቄዎች በአንጭሩ ከተገለጸ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው የጤና ስርዓት ይሻሻል የሚል ነው።
በዝርዝር ሲቀመጥም የህክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ክብር የማይሰጥ፡ ጥቅማቸውን የማያከብር ነው ይላል።
በአዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችም የአርሲውን ጥቃት በማውገዝ መንግስት ያረጀውንና የጤና ባለሙያዎችን ጥያዎች የማይመልሰውን የጤና ፖሊሲ እንዲቀይር ጠይቀዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች እየተነሳ ያለውን ጥያቄ አስመልክቶ በቲውተር ገጻቸው ምላሽ የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ላለፈው አንድ ዓመት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራን ነው ሲሉ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ከሁሉም የጤና ባለሙያዎች፣ ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከሙያ ማህበራት ጋር በመሆን በህክምና ባለሙያዎቹ የተነሱትን ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የመወያያ መድረኮች መዘጋጀታቸውን ነው ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን የገለጹት።