የህሊና እስረኞች ድብደባ ተፈጸመባቸው
(ኢሳት ዜና ግንቦት 02 ቀን 2010 ዓ/ም) በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ የክስ መዝገብ ተከሰው ከሚገኙት እስረኞች መካከል የተወሰኑ እስረኞች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል። ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓም በዋለው ችሎት ተከላከሉ የተባሉት ተከሳሾች ያሰሙትን ተቃውሞ ተከትሎ የእስር ቤት ፖሊሶች በተከሳሾች ላይ ድብደባ የፈጸሙባቸው ሲሆን፣ በድብደባው ብዛት አንዳንዶች አካላቸው ተጎድቷል።
11 ተከሳሾች ደግሞ በቅጣት መልክ ጨለማ ቤት እንዲታሰሩ ተደርጓል። እስረኞቹ ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ የምግብ አድማ በማድረግ ላይ ናቸው። ዛሬ ግንቦት2 ቀን 2010 ዓም የተወሰኑ እስረኞችን ወደ ዝዋይ ለመጫን በተደረገው ሙከራ በእስር ቤት ውስጥ ውዝግብ ተነስቶ እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል። ሚያዚያ 30 በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ጠባቂዎች የታሳሪ ቤተሰቦችን እና ታዳሚዎችን በመሳሪያ ሲያስፈራሩ እንደነበር፣ ችሎት ውስጥ የተወሰኑ እስረኞችንም መደብደባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።