(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 5/2011) የሃይማኖት አባቶች ጎሰኝነትን ከማራገብ እንዲቆጠቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ ከሃይማኖትአባቶችና ምሁራን የተውጣጣውን ስብስብ ባነጋገሩ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎችመጽሀፍ ቅዱስ በአንድ እጃቸው በሌላኛው ደግሞ የጎሳ ፓለቲካን የሚያቀነቅኑ የሃይማኖት አባቶች ጉዳይ አስቸግሮናል ሲሉ ገልጸዋል።
ሰላም እየታጣ ነው፣ ሀገራችን ውሎና አዳሯ እሳት ማጥፋት መሆኑ አሳሳቢ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ለማ።
የሃይማኖት አባቶቹ ትዕግስት አስፈላጊ ቢሆንም ሀገር እንዲህ በሰላም እጦት በምትሰቃይበት ወቅት የመንግስት ትዕግስት የበዛ ሆኗል ሲሉ ወቅሰዋል።
አቶ ለማ መገርሳ ከሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ጋር ባደርጉት ውይይት ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ብርቱ ፈተና አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶቹና ምሁራን የሰላም ዕጦቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸው የመንግስት ትዕግስት በዝቷል ነው ያሉት። ትንሽ ቁንጥጫ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ አንድም ችግር የሆነባቸው የሃይማኖት አባቶች ሚና መሆኑን አንስተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች ጎሰኝነትን ያራምዳሉ ሲሉም ነው የተናገሩት።