የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰላምና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጀመረች

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 5/2011)የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሃገሪቱ እየታየ ያለውን አለመረጋጋትና ግጭት ለማስቆም በሚል በመላ ኢትዮጵያ የሰላምና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጀመረች።

በመላ ሀገሪቱ 52 አህጉረ ስብከት የሚዳረሱበት ይህው የሰላምና የወንጌል ዘመቻ ለአንድ ወር የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተሰማሩት የዘመቻው አባላት በ5 ቡድኖች የተከፈሉና እያንዳንዳቸው በሊቀጳጳስ የሚመሩ እንደሆነ ከቤተክህነት አካባቢ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ለዚህ ሃገር አቀፍ የሰላምና የወንጌል ዘመቻ 10 ሚሊየን ብር መመደቡም ታዉቋል።

በ5ቱ ቡድኖች በጠቅላላው 250 አባላት ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ይሰማራሉ።

እስከ ታህሳስ 26 የሚቆየው የሰላምና የወንጌል ተልዕኮ ዘመቻ ኢትዮጵያን በጽኑ እየተፈታተናት ያለውን የሰላም እጦት ተቀዳሚ አጀንዳው እንደሚያደርግ ከቤተክህነት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በ5 ሊቃነጳጳሳት የሚመራው የተልዕኮው ዘመቻ አባላት በ52ቱ ሃገረ ስብከቶች ተከፋፍለው ህዝባዊ ውይይትና የስብክት ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ተገልጿል።

ሰሞኑን ተልዕኮውን አስመልክቶ በቤተክህነት ጽሕፈት ቤት በተሰጠ ማብራሪያ ላይ እንደተመለከተው በአገር ሰላም እና በሕዝብ አንድነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩት የውይይት መርሐ ግብሮች፣ ከቤተ ክርስቲያን ምእመናን ውጭ የሆኑ ዜጎች የሚሳተፉበት ሕዝባዊ አቀራረብና ይዘት የሚኖረው መድረክ ቡድኖቹ በየተሰማሩባቸው አህጉረ ስብከቶች የሚያከናውኑት ይሆናል።

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ለኢሳት እንደገለጹት ለአንድ ወር በሚዘልቀው የሰላምና የወንጌል ስብከት ዘመቻ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰላም እጦት በትኩረት የሚታይ ይሆናል።፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለውና በቀላሉ የሚገታ የማይመስለው የሰላም እጦት ችግር አሳስቦኛል ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሃገር አቀፍ የሰላምና የወንጌል ስብከት ተልዕኮ እንዲካሄድ የወሰነው  ባለፈው ጥቅምት 14 ቀን 2011 መሆኑ የሚታወስ ነው።

ቤተ ክርስቲያኒቱ በሰላም እጦት የሚገጥሟትን ችግሮች የምትቋቋምበትና ለሀገራዊ እርቅና ለሕዝብ አንድነት መጠበቅ ያላትን ታሪካዊና ብሔራዊ ሚና የምትወጣበት ተልዕኮ እንደሚሆንም ቅዱስ ሲኖዶሱ አስታውቋል።

ትላንት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና የወንጌል ስብከት ዘመቻ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን እንዲያሳይ ቤተክህነት ጥሪ አድርጋለች።

ለዚህ ዘመቻ በአጠቃላይ 10ሚሊዮን ብር መመደቡንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።