የሃዋሳ ፔፕሲ ኮላ እና የድሬደዋ ኮካ ኮላ ፋብሪካዎች  እንዲዘጉ ተደረገ

ታኅሣሥ ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የሃዋሳው ፔፕሲ ኮላ እና የድሬደዋ ኮካ ኮላ ፋብሪካዎች ተዘግተው ለሽያጭ የተስራጩት ምርቶቻቸው እንዲሰበሰቡ ሲል ንግድ ሚንስቴር የእገዳ ትእዛዝ መመሪያ አውጥቷል። የሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ንብረት የሆነው የሃዋሳ ፔፕሲ ፋብሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ቦትሊንግ ንብረት የሆነው የድሬዳዋው ኮካ ኮላ ምርቶቻቸው የጥራት ደረጃቸውን ሳይጠብቁ  ለተጠቃሚው ለገበያ መቅረባቸውን ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።

የሃዋሳ ሚሊኒየም ፔፕሲ ፋብሪካ በ2007 የተገነባ ሲሆን 500 ሰራተኞችን ያስተዳድራል። የሰራተኞቹ የስራ ዋስትናን በተመለከ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። የምርት ምዘና ማረጋገጫ ዳሬክተር የሆኑት አቶ ተኬ ብርሃን ስለ ፋብሪካዎቹ የጥራት ጉድለት እና መዘጋት አስመልክቶ ፎርቹን ላቀረበላቸው ጥያቄ ”የምርት ጥራት ጉድለት ምርመራዎችን በሁለቱም ፋብሪካዎች ላይ እያደረግን ነው። አሁን አስተያየት ለመስጠት ጊዜው ገና ነው” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከሃዋሳው ሞሃ ለስላሳ መጠጦች ምርቶች ላይ የተወሰደው የምርመራ ናሙና እንደሚያሳየው በምርቶቹ ላይ የጥራት ጉድለት ታይቷል። የሃዋሳ ሞሃ ለስላሳ ምርቶች የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃዎችን ያላሟላ መሆኑንም ድርጅቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ከሶስት ዓመት በፊትም ተመሳሳይ የጥራት ጉድለት በፋብሪካው ምርቶች ላይ ተከስቷል።

የፔፕሲ ምርቱ አሲድ እና ሲትሪክ ጁስ 2.5 PH መሆን ሲገባው የናሙና ምርመራው ውጤት ግን 2.43 PH ያሳያል። ይህም ዝቅተኛ የሆነ PH መጠን በለስላሳ መጠጦቹ ውስጥ መኖሩ በተጠቃሚው ጤና ላይ የጥርስ ኤናሜል ጉዳትን ጨምሮ የአጥንት መሳሳትን  የመሳሰሉ  አሉታዊ የሆነ የጤና መቃወስ ያስከትላል። በደቡብ ጤና እና የጤና ተዛማጅ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ዳርጌ ለፎርቹን ጋዜጠኛ እንዳሉት ”የሞሃ ምርቶች  የኬሚካል ደረጃቸው ከ1 እስከ 10 በመሆኑ  የዓለም የጤና ድርጅትን መስፈርት አያሟሉም። የፔፕሲ፣ ሚሪንዳ፣ ቶኒክ ሚሪንዳ እና አፕል ሚሪንዳ ምርቶች የናሙና ምርመራ እንደሚያሳየው ምርቶቹ ለጤና ጎጂ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል። ይህን ተከትሎ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በተሰጠ ቀጥተኛ ትእዛዝ ፋብሪካዎቹ ከሁለት ሳምንት በፊት እንዲዘጉ ተደርጓል።

ሞሃ ለስላሳ መጠጦች በሃዋሳ በአንድ ሰዓት ውስጥ 36 ሽህ 300 ሚሊ ሌትር ጠርሙስ ምርቶችን በማምረት ለገበያ ያቀርብ ነበር። ድርጅቱ እስካሁን  25 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቋል።

ኢስት አፍሪካ ቦኦትሊንግ ኮካ ኮላ በበኩሉ በድሬዳዋ ከተማ ብቻ  20 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ጋዜጣው ዘግቧል።