መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ ጀማል ዳውድ ካለፉት 8 ቀናት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን፣ ለእስር የዳረገውም መልእክቶችን በሞባይል ስልክ ልኸሃል ተብሎ ነው።
ይሁን እንጅ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች እንደገለጹት ጋዜጠኛ ጀማል የታሰረው በክልሉ ውስጥ የሚታየውን ዘረኝነት አጥብቆ በመቃወሙና ሌሎችን ጋዜጠኞች ታነሳሳለህ ተብሎ ነው።
የክልሉ ፖሊስ አደገኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና የተዛባ ዜና በመጻፍ ወንጀል ለመክሰስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ለማወቅ ተችሎአል።
ጋዜጠኛ ጀማል በክልሉ ኤፍ ኤም ራዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በክልሉ ጋዜጣ ላይ ዝግጅቶችንና ጽሁፎችን ያዘጋጅ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉ መንግስት ህዝቡ ቤታቸው በእሳት ለተቃጠለባቸው ሰዎች ድጋፍ በሚል የገንዘብ መዋጮ እንዲያወጣ እየተገደደ ነው። ህዝቡ በበኩሉ ገንዘብ ብናወጣ ተጎጂዎች እጅ ላይ አይደርስም በማለት ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ የታሰሩ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ታውቋል። የክልሉን ፖሊስ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሰካም።