የሃሙሲት ነዋሪዎች ገዢው ፓርቲ እየተበቀለን ነው ይላሉ

ጥር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከባህርዳር 30 ኪሚ ርቃ በምትገኘው በደቡብ ጎንደሩዋ ሃሙሲት ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ገዢው ፓርቲ እየተበቀለን ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ሲያደርግ በነበረው ጦርነት ሃሙሲት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህም በቀል ይመስላል ይላሉ ነዋሪዎች ፣የህወሃት የደህንነት ሰዎች በከተማ ውስጥ አሉ የሚባሉ ታላላቅ ሰዎችን ከመግደል ጀምሮ አፍነው ወስደዋቸዋል።

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ አንድም መሰረተ ልማት የሚባል ነገር እንዳልሰተራላቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የቧንቧ ውሃ  የሚያገኙት በዛ ከተባለ በወር አንድ ጊዜ ነው። አብዛኞቹ ነጋዴዎች በግብር የተነሳ ከተማዋን እየለቀቁ ሄደዋል።

ከሁሉም በላይ ይላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በ1950 ዎቹ የተሰራው የሃሙሲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አይነት ጥገና ሳይደረግለት የከተማዋ ብቸኛ ትምህርት ቤት ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ትምህርት ቤቱ እየፈረራሰ መገኘቱ ያሳሰባቸው ነዋሪዎች ገንዘብ አዋጥተው ለማስጠገን ሙከራ ቢያደርጉም፣ በአስተዳዳራዊ ጫናዎች ምክንያት አልተሳካለቸውም።

በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በማቋረጥ የአደንዛዥ እጾች ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን በማሰስታወስ ኢሳት ለሚመለከተው አካል አቤት ይበልልን ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሃሙሲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዋቂዋን ድምጻዊ አስቴር አወቀን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ታዋቂ ሰዎችን ማፍራቱን ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።

የከተማዋን አስተዳዳሪዎች ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።