(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 29/2011) በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ከ20 አመት በፊት ተዘግቶ የቆየው የሁመራ አምሃጀር ድንበር የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተከፈተ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ እንዲሁም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በተገኙበት የሁለቱ ሃገራት ድንበር ተከፍቷል።
የሁለቱ ሃገራት ድንበር በይፋ መከፈቱን የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ሪቫን በመቁረጥ አብስረዋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች በሐምሌ 2010 አስመራ ላይ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ቀደም ሲል ሌሎች አዋሳኝ ድንበሮች መከፈታቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሃገራት ድንበር መከፈትን ተከትሎ ከፍተኛ ሕዝባዊ እንቅስቃሴና የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ቆይቷል፡
ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በሚል ኤርትራ በተለይ በዛላአምበሳ በኩል ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አስመራ ላይ ባደረጉት ስምምነት የሁለቱ ሃገራት የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መስማማታቸው ይታወቃል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ ወደ አስመራ በረራ መጀመሩም አይዘነጋም።