በምዕራብ ጉጂ የሰላም ሳምንት ጥሪ ቀረበ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 29/2011)በምዕራብ ጉጂ አባገዳዎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የሰላም ሳምንት ጥሪ አደረጉ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ከሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በሁለተኛ ደረጃ በምትጠቀሰው የምዕራብ ጉጂ ዞን የተጠራው የሰላም ሳምንት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍበት በሚል የተዘጋጀ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ፋይል

በአዶላ ከተማ የሚካሄደው የሰላም ጉባዔ የሰላም ሳምንቱ ዋነኛ ክንውን እንደሆነም ተገልጿል።

ፌስቡክን ጨምሮ በማህበራዊ መድረኮች ሳምንቱ ስለሰላም በመስበክ ህዝቡ ስሜቱን እንዲገልጽ በአባገዳዎች በኩል መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል።

የሰላም ሳምንቱ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚከናወንም ከወጣው መርሃግብር መረዳት ተችሏል።

ምዕራብ ጉጂና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎች ሰላም ከራቃቸው አመት አለፋቸው።

የኦነግ ጥቃት፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ግድያና ዘረፋ ሳይለይዋቸው ወራት ተቆጠሩ።

ከአጎራባች የደቡብ ክልል አካባቢዎች ጋርም የተፈጠረው ግጭት ቀጠናውን የቀውስ አድርጎት ቆይቷል። አሁንም አልበረደም።

ከ7ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን በማስተናገድ በሀገራችን ታሪክ የሃገር ውስጥ ስደት በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገበበት አካባቢም ነው።

ከጌዲዮ ብሔረሰብ ጋር የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት ጠባሳው ሳይሽር እንደአዲስ እየተቀሰቀሰ መሆኑን ጉዳዩውን ውስብስብ አድርጎታል።

የኦነግ ታጣቂዎችም ከምዕራብ ጉጂ እየተንደረደሩ የአማሮ ኬሌን አካባቢዎች በመዝረፍ፣ ማሳ በማቃጠልና ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል የቀውሱ መሪ ተዋናይ ሆነው ብቅ ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በምዕራብ ጉጂ በኦነግ ታጣቂዎች የባንክ ገንዘብ ለመዝረፍ ሙከራ ተደርጓል።

ሶስት የወረዳ አመራሮች ታፍነው ተወስደዋል። በትንሹ 5 የኮሬ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተነሳ ግጭት የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጧል።

በፊንጭ ውሃ በመከላከያ ሰራዊት በተወሰደ ርምጃ በትንሹ 10 ሰዎች ተገድለዋል።

ምዕራብ ጉጂ ባልተለመደ ሁኔታ ሰላም ደፍርሶባት የነዋሪዎቹ የጭንቀት ምድር ሆናለች።

ፌደራል መንግስቱ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመሆን ርምጃ መጀመሩን አስታውቋል።

በዘላቂነት የምዕራብ ጉጂን ቀውስ ለማርገብና ለማጥፋት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ በምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኙ አባገዳዎች ከዛሬ ጀምሮ  ሳምንቱ የሰላም እንዲሆን ጥሪ ያደረጉት።

የፊታችን እሁድ የሚጠናቀቀው የሰላም ሳምንት ለምዕራብ ጉጂ በተናጠል፣ ለሃገሪቱ ደግሞ እንደ አጠቃላይ ሰላም የሚነፍስባት ወረዳ፣የትጥቅ ትግል የሚቆምበት፣ ጠመንጃ የሚወገዝበት መልዕክት የሚተላለፍበት እንደሚሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሳምንቱን ስለሰላም አብዝተው እንዲመክሩበት ጥሪ ያደረጉት አባገዳዎች ሁሉም ወገኖች ከጸብ ጫሪነት እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።