የሁለቱ ሲኖዶሶች የሰላምና አንድነት ጉባኤ እንደቀጠለ ነው

ህዳር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ረቡእ ሕዳር 26፡ 2005 የተጀመረው ስብሰባ በዛሬው እለት ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎ እንደዋለ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመለከተ።

ስብሰባው እስከእሁድ ፕሮግራም የተያዘለት ቢሆንም፤ ምናልባት ከእሁድ በፊት በዛሬው እለት ውጤቱ ሊታወቅ ይችላል ሲሉ አንዳንድ ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያው ልኡካን ዳላስ በደረሱበት እለት ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ለፓትሪያርክ መርቆሬዎስ የጻፉትን ደብዳቤ ተከትሎ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ትኩረትንና ውይይትን ጋብዘዋል።

ፕሬዚዳንቱ፤ ፓትሪያርክ መርቆሬዎስ ወደመንበራቸው አንዲመለሱ የጋበዙበትን ደብዳቤ አንስተው፤ በምትኩ አገርቤት ገብተው እንደማንኛውም ጳጳስ ለምርጫ መወዳደር ይችላሉ በሚል ደብዳቤ እንደሚለወጥ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ ለአሜሪካን ድምጽ ተናግረዋል።

ከሀገር ቤት በመጡትና በውጪ በሚገኙት አባቶች መካከል ሰላማዊ በመሆነና በመግባባት መንፈስ በቀጠለው በዚህ ስብሰባ፤ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው በተነሱበት ሂደት ላይ መወያየታቸው ታውቋል።

አሁን እርሳቸው ወደሀገር ቤት እንዴት ይመለሱ በሚለው ሁኔታ ላይ እየመከሩም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።