የሁለቱም ሀይማኖት ተከታዮች ከመንግስት እኩይ ሴራ እንዲታቀቡ ጥምረት አሳሰበ

ሚያዚያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-ጥምረት ለነጻነት፡ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ  ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደጠቀሰው መለስ ዜናዊ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ያነሱትን የመብት ጥያቄ ክብደት ስጥቶ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በማንቋሸሽና በማናናቅ በአለም ከሚታየው አክራሪ ሂደት ጋር በማገናኘት የምእራቡን አለም ቀልብ ለመሳብና ለዲፕሎማሲያዊ ፍጆታ ሊጠቀምብትም  ላይ ታች እያለ ነው።

ወያኔ በጠመንጃ ኃይል ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ሲሰራበት የነበረው ህዝብን በዘር የመከፋፈልና የኢትዮጵያን አንድነት የማናጋት ሴራው እየከሰመ ስለመጣበት ህዝቡን በሃይማኖት ቅራኔ ውስጥ በመዝፈቅ የአገዛዝ እድሜውን ለማራዘም እየተፍጨረጨረና እየማሰነ ይገኛል ያለው ጥምረት፣  በቅርቡም የዘረኛው ስርአት መሪ መለስ ዜናዊ ሃይማኖትን በሚመለከት ለአሻንጉሊት ፓርላማዉ ያቀረበው ሀተታ እጅግ አደገኛ ነው ብሎአል።

ጽንፈኝነት በእስላሙም ሆነ በክስርስትያኑ መካከል እየታየ ነው በማለትና በእንጭጩ መቅጨት በሚል ዘይቤ በሰላም አብረው በመኖር የሚታወቁትን የክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለማጋጨትና በዚህም ሳቢያ የመብት ጥያቄዎችን በሃይል ለመደምሰስ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ከቅርብ ቀናት በፊት በአርሲ በእስልምና ተከታይ ኦሮሞ ወግኖቻችን ላይ የወሰደው የጭፍጨፋ እርምጃ ይህን የሚያረጋግጥ ነው ሲል ጥምረቱ አክሏል።

የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በሁለቱም ዋና ዋና ላይ ሃይማኖች ላይ በጠላትነት የተነሳ መሆኑን የቅርብ ሳምንታት ተግባሩ ጉልህ ማስረጃ ስለሆነ የሁለቱም ሃይማኖቶች ተከታዮች ይህን እኩይ ሴራ ተገንዝበው የወያኔ ተንኮል መሳሪያ እንዳይሆኑ ጥምረት በአጽኖት ያሳስባል ብሎአል።

የሁሉም ጠላት የወያኔ ዘረኛ ስርዓት ስለሆነ ይህን ግፈኛና ከፋፋይ ስርአት ከስር መሰረቱ ለመፈንቀል በህብረት መታገል ከሁሉም ኢትዮጵያዊ  የሚጠበቅና ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚሻ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ያለው ጥምረት ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጳያዊ ዜጋ ለሀገር አንድነትና ለህዝብ መብቶች መከበር እንዲሁም ለነጻነትና ለፍትህ ከዳር እስከ ዳር እንዲነሳ ጠይቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide