የሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ- ከድርጅቱ ሊቀመንበር ከአቶ ኦርዲን በድሪ ጋር እየተጋጩ መሆኑ ተነገረ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) ፕሬዚዳንቱ አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ ከድርጅታቸው ሊቀመንበርነት መነሳታቸውን ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት ኃላፊነታቸውን ባለማንሳቱ ምክንያት- አዲስ ከተሾሙት የሐብሊ ሊቀመንበር ከአቶ ኦርዲ በድሪ ጋር በተደጋጋሚ ግዜያት እንደሚጣሉ የድርጅቱ የቅርብ ምንጮች ተናግረዋል። አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ የክልሉን ካቢኔ አባላት ለአንድ ወር ጉብኝት ወደ ቻይና በመላካቸው አቶ ኦርዲን ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠርም የስልጣን ግዜያቸውን ለማራዘም መሞከራቸውን እየነቀፉና እየተቃወሙ ነው። ክልሉን የሚመሩት መሪዎች እርስ በርስ ባለመስማማታቸውም- በህዝቡ ሰላምና ኑሮ ላይ ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ።
አቶ ሙራድ በቅርቡ ለኢሳት ሲናገሩ ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ የድርጅታቸው አባላት ስላስገደዱዋቸው በስልጣን ላይ ለመቆየት መገደዳቸውን ገልጸው ነበር።
የሃብሊ ባለስልጣናት የእርስ በርስ ውዝግብ በተደራቢነት ክልሉን ከሚያስተዳድረው ኦዴፓ ጋርም ተስማምቶ ስራዎችን ለመስራት እንዳላስቻለና ክልሉ ፈጣን ለውጥ እንደሚፈልግ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱንም ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።