ሰኔ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፌስ ቡክ ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን በመጻፍ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ደጋፊ ያገኙት ዞን 9 እየተባሉ የሚጠሩ ወጣት ጸሃፊዎችና ጋዜጠኞች ባለፈው ቅዳሜ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም፣ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ወደ ማእከላዊ ተመልሰዋል።
እጆቻቸውን በካቴናዎች የታሰሩት ወጣት ብእረኞች አካላዊ መጎሳቆል ቢታይባቸውም፣ መንፈሳቸው ግን ጠንካራ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
መንግስት በፌስ ቡክ እና በተለያዩ የማህበራዊ የመገናኛ መንገዶች የሚሰራጩ መረጃዎችን ለማዛባት ወይም ለመቆጣጠር ከፍተኛ ባጀት መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ታዛቢዎች እንደሚሉት እያንዳንዱ የመንግስት መረጃን እና መረጃ ሰጪዎችንና ተንታኞችን ለማፈን የሚሄድበት እርምጃ አዳዲስ ጸሃፊዎች እንዲወለዱ እያደረገ ነው።