ፈንጅ አምካኝ ወታደሮች በብሄራችን የተነሳ አድሎ ተፈጽሞብናል ሲሉ ተናገሩ

ሰኔ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዩ ኤርትራ  ጦርነት ወቅት ፈንጅ ያመክኑ የነበሩ  ወታደሮች እስከዛሬ ለከፈልነው መስዋትነት ከ3 እስከ 7 ሺ ብር ብቻ እየተሰጠ፣ ብሄራችን እየተመረጠ ከመከላከያ እንድንሰናበት ተደርገናል ብለዋል።

ሰሞኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት  ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ተክለብርሃን ወ/ዓረጋይ ወደ አማራ፣ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች ተዘዋውረው ወታደሮችን ያነጋገሩ ሲሆን “ጊዜው ለልማት እና ለስራ የሚነሳሱበት እንጅ አድማ በመምታት ነገር የሚያሰሩበት አይደለም” በማለት አስጠንቅቀዋቸዋል።

“የግፍ ግፍ ተፈፅሞብናል” ያሉት ፈንጅ አምካኝ ወታደሮች፣  ከፍተኛ መስዋትነት የከፈልነው የአማራ  ኦሮሞ እና ደቡብ ብሄር ተወላጆች ከስራ እየተሰናበትን የህወሃት አባላት አዲስ ምልምል ወታደሮች የስራ እድል እየተሰጣቸው ነው በማለት በተለይ በሰላም አስከባሪ ስም እየተፈጸመ ያለውን አድልዎ በማንሳት ተቃውሞቸውን አሰምተዋል፡፡

200 የሚደርሱ በአባይ ግድብ ተቀጥረው እንዲሰሩ የተደረጉ ፈንጅ አምካኞች “አታስፈልጉም” ተብለው መባረራቸውንም አውስተዋል፡፡

በሶስቱ ክልሎች መስዋትነት ከፍለን በብሄራችን የተነሳ ከስራ ተባረርን የሚሉ 513 ፈንጅ አምካኝ ወታደሮች አሉ።

ከደህንነት ክፍል የተገኙው መረጃ እንደሚያሳየው መንግስት የሶስቱ ክልል ፈንጅ አምካኝ ተወላጅ ወታደሮች ላይ ጥብቅ ስለላ እና ክትትል የሚያደርግ ሲሆን ፣ ከድተው በትጥቅ ትግል የሚታገሉትን ተቃዋሚዎች ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለው።