ሚያዚያ ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው የ10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ፣ ጸሃፊ ዘላለም ክበረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃነና ኤዶም ካሳየ አርቲክል 19 እየተባለ ከሚጠራው ይውች ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የግብጽ፣ የኤርትራ መንግስትንና የግንቦት7 ትን ተልእኮ ለማስፈጸም ይንቀሳቀሱ ነበር የሚል ክስ ሊመሰርትባቸው እንደሚችል ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል።
መንግስት ወጣቶቹ የቀለም አብዮት ለማስነሳት ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ገንዘብ እንደተቀበሉ አድርጎ በማቅረብ ፣ በሽብረተኝነት ከተፈረጁት ድርጀቶች ጋር ግንኙነት በመመስረት ወንጀል ሊከሳቸው ማሰቡ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስር ላይ የሚገኘውየሙስሊሞችጉዳይመጽሄት አዘጋጅ ጋዜጠኛሰለሞንከበደ ለብይን ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ዳኛ የለም በሚል ምክንያት ለሰኔ 26 ተቀጥሯል። ጋዜጠኛው ከዚህ ቀደምም ዳኛ የለም በሚል ምክንያት ብይን ሳያገኝ ተመልሷል።
በአዳማ ከተማ የተያዙ ሙስሊሞችም እንዲሁ ለአራት ወራት በከፍተኛ ስቃይ በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ከተደረገ በሁዋላ ዛሬም ዳኛ የለም በሚል ጉዳያቸው ሳይታይ ወደ ቃሊቲና ቂልንጦ እስር ቤቶች ተመልሰዋል።