የካቲት 5 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-10 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዛምቢያ በሊበርቪሌ ጋቦን ተዘጋጅቶ የነበረውን የአፍሪካ ዋንጫ አይቮሪ ኮስትን በፍጹም ቅጣት ምት 8 ለ7 በሆነ ውጤት አሸንፋ ዋንጫውን ወስዳለች።
የዛምቢያው አሰልጣኝ ሄርቪ ሪናርድ ዋንጫ በ1993 በአውሮፕላን አደጋ ለተሰውት የዛምቢያ ተጫዋቾች መታሰቢያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ከ19 አመት በፊት የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሴኔጋል ሲያመራ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በተዘጋቸበት በጋቦን በተከሰተ የአውሮፕላን አደጋ ማለቁ ይታወሳል።
“አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አገር ለዋንጫ ከደረስን ፣ ከፍተኛ የሆነ ትርጉም እንዳለው ለተጫዋቾች ነግሬያቸው ነበር። ጥንካሬውን ከየት እንዳመጡት አላውቅም፣ አሳኩት” ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
90 ሚሊዮን ያላት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ካቃታት 30 አመት ሞልቷታል።
አቶ መለስ ዜናዊ ከ20 አመት በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ፣ አንድ ስታዲየም ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስገነባሉ ተብለው ሲጠየቁ፣ ተበድረን ስታዲየም ከምንገነባ ተበድረን ማዳበሪያ ብንገዛ እንመርጣለን ብለው ነበር።
ባለፉት 20 አመታት ወይ ዋንጫውን ወይ በማዳበሪያ የተመረተውን ዳቦ አላየንም የሚሉ አስተያየቶች በብዛት ይሰማሉ።