መድረክ በሊዝ አዋጁ ዙሪያ በጠራው ስብሰባ ላይ በርካታ ህዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል

የካቲት 3 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፈው ሳምንት አንድነት ፓርቲ በጠራው ውይይት ላይ የተገኘው ህዝብ ከአዳራሹ አቅም በላይ መሆን፣ የነገውን የመድረክ ስብሰባ የአዘጋጁትን ወገኖች አሳስቦዋቸዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመድረክ አባል ለኢሳት እንደተናገሩት በቀድሞው ቀበሌ 42 በአሁኑ ወረዳ 5 የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ በርካታ ህዝብ እንደሚገኝ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ የራሱን ሰዎች አብዛኛውን ቦታ እንዲይዙት በማድረግ ውይይቱን ለማጨናገፍ ሊሞክር ይችላል ሲሉ ባለፈው ሳምንት በአንድነት ስብሰባ ላይ የተበተነውን ወረቀት በማስታወስ ስጋታቸውን ገልጠዋል።

መድረክ በቅርቡ የወጣውን የሊዝ አዋጅ እንደሚቃወመው ፣ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ ለኢሳት ተናግረዋል

አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር የመሬት ፖሊሲው ያስፈለገበትን ምክንያት መናገራቸው ይታወሳል። ከጥንት ጀምሮ በነባር ይዞታነት የተያዙት መሬቶች ወደ ሊዝ የሚገቡት ሲሸጡ ብቻ መሆኑን አቶ መለስ መናገራቸው ይታወሳል።

ውሳኔው በርካታ ነባር ይዞታ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚያድርግ ነው የሚሉ ትችቶች በብዛት ይቀርባሉ።