ጥቅምት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በሶማሊ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ የሚታየው ሁኔታ እስከ ዛሬ ከታዩት ሁሉ የተለየ ነው ይላሉ ነዋሪዎች። ከሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ወደ ከተማው መግባት ወይም ከከተማው በመውጣት ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሄድ የተከለከለ ነው ይላሉ።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማው በብዛት በመገኘት ቤት ለቤት የሚያካሂዱት ፍተሻ ለነዋሪዎች ጭንቀትን ፈጥሮባቸዋል። በክልሉ ፕሬዚዳንት ትእዛዝ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ላፕቶፕ ኮምፒዩተራቸውን ተቀምተዋል። ባለስልጣናቱ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ለምን እንደፈለጉ ባይናገሩም የከተማዋ ነዋሪዎች ግን፣ መንግስት መረጃ አገኛለሁ በሚል መውሰዱን ይናገራሉ።
አልሸባብ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል በማለት የጸረ ሽብር ግብረሀይል መግለጫ ካወጣ በሁዋላ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በሰጠው ትእዛዝ ይህንን ሰበብ አድርጎ ምንም አይነት እቃ ከጅጅጋ እንዳይወጣ ወይም ወደ ጅጅጋ እንዳይገባ ለማድረግ ከፍተኛ ፍተሻ እየተካሄደ ነው።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም በአልሸባብ ስም በክልሉ ነዋሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አውግዟል።
ጅጅጋ በመጪዎቹ ሳምንታት የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን እንደምታከብር ይታወቃል።