መጋቢት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ወደ አረብ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ የሚደረገው ጉዞ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከአንድ ዓመት በፊት ከታገደ በሃላ ሕገወጥ ዝውውሩ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የሥራ ስምሪት ህጉ እስኪስተካከል ድረስ ለስድስት ወራት ብቻ ጉዞው እንዲታገድ መንግሥት ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ እገዳው ሳይነሳ ከአንድ ዓመት ከአራት ወራት በላይ አስቆጥሮአል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩት ድርጅቶችም አብዛኛዎቹ ከእገዳው ጋር ተያይዞ ለቢሮ ኪራይና ለሰራተኞች ወጪ በማድረጋቸው ለኪሳራ በመዳረጋቸው ምክንያት ከሥራው ለመውጣት የተገደዱ ሲሆን፣ ይህ በመንግሥት የተፈጠረ ክፍተት ደግሞ በሕገወጥ መንገድ በድንበሮችና የጎረቤት ሀገራትን እንደመተላለፊያ በመጠቀም ሰዎችን ለሚያዘዋውሩ ሕገወጦች መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ታውቆአል፡፡
ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹ በአንድ ሰው ከ10 አስከ 40 ሺህ ብር በመቀበል ወደተለያዩ የአረብ ሀገራት በተለይ ኬንያንና ጅቡቲን መሸጋገሪያ በማድረግ ሴት የቤት ሠራተኞችን በማስወጣት ላይ መሆናቸው በኢትዮጵያዊኑ ላይ የሚደርሰውን እንግልት አባብሶታል፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን በስራ ላይ ያለውን አዋጅ በማሻሻል በውጪ ሀገር ስራ ስምሪት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን እቀርፋለሁ ቢልም፣ ያቀደውን ማሳካት ባለመቻሉ በተቃራኒው ሕገወጥ ዝውውር እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማድረጉ እንዳሳዘናቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ከሁለት ወራት በፊት ባወጣው የ2014 ሪፖርት ሕገወጥ ዝውውሩ መባባሱን በመጠቆም በርካታ ኢትዮጽያዊያን ወደመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት ሲሰደዱ ጅቡቲ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ እና የመንን እንደመሸጋገሪያ እንደሚጠቀሙ አስታውቆአል፡፡
በመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት በቤት ሠራተኝነት የሚቀጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች አብዛኛዎቹ ለጉልበት ብዝበዛና ለወሲብ ባርነት ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ ድብደባ፣ አልፎ አልፎም ግድያ ይፈጸምባቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የተቀመጡትን ዝቅተኛ መስፈርቶች ማሟላት አልቻለም ሲል ስቴት ዲፓርትመንቱ በይፋ መውቀሱ ይታወቃል።