ወደ ቤተ መንግስት ያለፈቃድ ያቀኑት ወታደሮች ዝርዝር ቅጣት ይፋ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 8/2011) ወደ ቤተ መንግስት ያለፈቃድ ካቀኑ ወታደሮች ውስጥ 66ቱ ላይ የተላለፈባቸው ዝርዝር ቅጣት ይፋ ሆነ።

ከነትጥቃቸው ያለፈቃድ ወደ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ካመሩት 200 የሰራዊት አባላት መካከል 66ቱ ላይ ከ5 እስከ 14 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

ፋይል

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከ500 ሰው በላይ በተገኘበት ግልጽ ችሎት  መታየቱ ታውቋል።

በውሳኔው መሰረት አንድ ተከሳሽ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሦስት ተከሳሾች በ13 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 11 ተከሳሾች በ12 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።

ሌሎች 12 ተከሳሾች በ11 ዓመት ጽኑ እስራት፣ አራት ተከሳሾች በ10 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 16 ተከሳሾች ከ9 ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ተላልፎባቸዋል።

            10 ተከሳሾች ከሰባት ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት፣ አምስት ተከሳሾች ከስድስት ዓመት ከስምንት ወር እስከ ስድስት ዓመት እና አንድ ተከሳሽ በአምስት አመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም ከ66ቱ በተጨማሪ ሌሎቹ የሰራዊት አባላት አስተዳደራዊ ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

ተከላካይ ጠበቃ ደሳለኝ ዳካ ተጠርጣሪዎቹ ከፍርድ እስከ ውሳኔ የነበረው ሂደት በህገመንግስታዊ መንገድ መካሄዱን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ጥፋተኛ በተባሉት ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ነው የታወቀው።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከ500 ሰው በላይ በተገኘበት ግልጽ ችሎት ነው።