ወታደራዊ እዙ በመተማ ዮሃንስ ያዘጋጀው ስብሰባ በተቃውሞ ተቋረጠ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ/ም) ባለፈው እሁድ መጋቢት 15/2010 ዓ.ም፣ በመተማ ዮሃንስ በቀበሌ 03 አዳራሽ ወታደራዊ እዙ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ከመተማ ህዝብ ጋር ለማድረግ የሞከረው ስብሰባ በከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት ስብሰባው ተቋርጧል።
ህዝቡ ፣ “የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ መልስ ያግኝ፣ ለሱዳን ተቆርሶ የተሰጠው የአባቶቻችን ርስት በአስቸኳይ ይመለስልን፣ በማስፈራራት ስልጣን ማራዘም አይቻልም” የሚሉና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ህዝቡ ጥያቄዎች ሲነሱ ድጋፉን በጭብጨባና በፉጨት የገለጸ ሲሆን፣ ጸጥታ ለማስከበር የተሳናቸው የመድረኩ መሪዎች የፌድራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት ጠርተዋል። ህዝቡም በብስጭት “ፍርሃት የዘራችን አይደለም” በማለት መድረኩን እረግጦ እንደ ወጣ የደረሰን መረጃ ያሳያል።
ስብሰባውን ከምዕራብ እዝ ኮ/ል ተሾመ የተባለ እንዲሁም የከተማው የአስተዳደርና ጸጥታ ሃላፊ አቶ ለምለሙ ባዬ መርተውታል።