በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳን ጨምሮ ውጥረት መንገሱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2010)በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳን ጨምሮ በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ውጥረት መንገሱ ተገለጸ።

ሞያሌ

ጨለማን ተገን አድርጎ በተደራጀ መልኩ በቅኝት ያሉና በወታደራዊ ደህንነቱ ውስጥ የሚሰሩ ወታደሮች በሚያመሹበት ስፍራ መገደላቸው ውጥረቱን እንዳባባሰው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ከሞያሌ 147 ተብሎ ከሚጠራው ካምፕ ወታደሮች እየጠፉ መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል በሰራዊቱ ውስጥ ከሃምሳ አለቃ በላይ ማዕረግ ላላቸው የበታች ሹሞች የመቶ አለቅነት ማዕረግ ሊታደላቸው መሆኑን የኢሳት የመከላከያ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የበታሹሞቹ  ለማዕረግ ዕድገት ፎርም መሙላት መጀመራቸው ታውቋል።

ለኢሳት በሚደርሱ መረጃዎች ላይ እንደተመለከተው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልፎ አልፎ በወታደሮች ላይ ተመሳሳይ በሆነ ጥቃት  የግድያ እየተፈጸመባቸው ይገኛል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ በአንድ ሌሊት 1 እና 2 የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸው እየተለመደ መጥቷል።

በተናጠልና እስከሁለት ሆነው ቅኝት በሚወጡ ወታደሮች ላይ የሚፈጸመው ግድያ በቅርቡ በሞያሌ የተፈጸመውን ጭፍጭፋ ተከትሎ በተደጋጋሚ መከሰቱን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ሁኔታው የካምፑን ወታደራዊ መሪዎች እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በተለይም ወታደራዊ ደህንነቶች በሚያመሹባቸው ቦታዎች የሚወሰደው ተደጋጋሚ የግድያ ርምጃ በአካባቢው ያለውን ውጥረት ይበልጥ እንዳጠናከረው ተገልጿል።

ሁኔታው ያሰጋቸው የካምፕ 147 ወታደራዊ አመራሮች አምስትና ከዚያ በላይ በቡድን የሆነ የቅኝት ግዳጅ እንዲሆን ማዘዛቸው ታውቋል።

ከዚሁ ጋርም ተያይዞ በሞያሌ አቅራቢያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማሰራጫ ተቋማት ፣በመንግስት ተቋማትና በወታደራዊ ካምፕ የሰፈሩ ወታደሮች ከግቢ እንዳይወጡ ጥብቅ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም 147 ተብሎ ከሚጠራው ካምፕ እና በሞያሌ ዙሪያ ከሚገኙ የጥበቃ ቦታዎች ወታደሮች እየጠፉ ነው ተብሏል።

ከሞያሌው ጭፍጨፋ ወዲህ በትንሹ አምስት ወታደሮች መጥፋታቸው የተገለጸ ሲሆን አዲስ ተደልድለው የመጡ ወታደሮችም በፍርሃት ቆፈን ተይዘው የማምለጫ መንገዶችን እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

ከካምፕ ከማምለጥ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አዲስ ድልድል ወታደሮች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን አንድ ወታደር ደግሞ በምሽት ተረኛ  ጥበቃ ወታደር ጥይት ተመቶ መገደሉ ታውቋል።

በሌላ በኩል በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከሃምሳ አለቃ በላይ ማዕረግ ላላቸው የበታች ሹሞች የመቶ አለቅነት ማዕረግ ሊታደላቸው መሆኑን የኢሳት የመከላከያ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በሰራዊቱ ውስጥ እየጎላ የመጣውን ተቃውሞ ለማጥፋት በሚል በአገዛዙ መሪዎች በገፍ መታደል የጀመረው ወታደራዊ የማዕረግ እድገት ቀጥሎ ከሃምሳ አለቃ በላይ ማዕረግ ላላቸው የበታች ሹማምንት  በሙሉ የመቶ አለቅነት ማዕረግ  እንዲሰጣቸው ተወስኗል።

በዚህም መሰረት ከሃምሳ አለቃ በላይ ማዕረግ ያላቸው የማዕረግ እድገት ቅጽ  መሙላት  ጀምረዋል።

ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ ለ62 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ከብርጋዴየር ጄነራልነት እስከ መሉ ጄነራል ማዕረግ የተሰጠበት ሁኔታ መነጋገሪያ እንደነበረ የሚታወቅ ነው።

የህወሀት ነባር አመራር የሆኑት አቶ አባይ ጸሀዬ የብሄረሰብ ኮታ ለማመጣጠን ብለን ችሎታ ለሌላቸው ሁሉ የጄነራልነት ማዕረግ ሰጥተናል ማለታቸው የሚታወስ ነው።