ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም አይሲስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት ለመቃወም በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ድርጊቱን ለማውገዝ በስፍራው ተገኝታ የነበረችው
ወ/ሮ ንግስት ወንዲፍራው ምክንያቱ ባልታወቀ ሰበብ ከ3 አመት ልጇ ጋር ግንቦት 19/2007 ዓ.ም ያለ ማዘዣ በፖሊስና በደኅንነት ኃይሎች ተወስዳ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰረች በሁዋላ ሰኔ 17/2007 ዓ.ም ቄራ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት
ቀርባ የ8 ወር እስራት ተፈርዶባታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሌላዋ ተከሳሽ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሜሮን አለማየሁ ከሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ሰልፍ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባት ሲሆን፣ ሜሮን ሰኔ 17/2007 ዓ.ም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጎፋ ምድብ ችሎት
በመቅረብ የ መከላከያ ምስክሮቿንም አቅርባ አሰምታለች፡፡ከአንድ ወር በላይ ዋስ ተከልክላ በእስር ላይ ቆይታ ከቀናት በፊት በዋስ ወጥታ ጉዳዩዋን በውጭ ሆና እየተከታተለች ያለችው ሜሮን፣ በቀረበባት ክስ ላይ ለብይን ሰኔ 24/2007 ዓ.ም
ቀጠሮ ተሰጥቷታል፡፡
ፍርድ ቤት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ጠርቶት ከነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ረብሻ አስነስተዋል ከተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መካከል እስካሁን በአራቱ ላይ የጥፋተኝነት ብይን በመስጠት እንዲታሰሩ የወሰነ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በእስር
ላይ ሁነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።