(ኢሳት ዜና–ህዳር 4/2010)ኮከብ የሌበትን የኢትዮጵያ ባንዲራ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመብራት ማማ ላይ ከፍ አድርጎ የሰቀለው ወጣት በፖሊስ ከታሰረ በኋላ አለመለቀቁ ተነገረ።
ባንዲራውን ሲያውለበልብ ያረፈደው ወጣት በፖሊስና በእሳት አደጋ ሰራተኞች በክሬን አማካኝነት ከማማው ላይ እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ ታስሯል።
በሌላ ዜና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሰቀለ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ ለማውረድ የሞከሩና ግቢውን ጥሰው በመግባታቸው የታሰሩት የዲሲ ግብረ ሃይል ሁለት አባላትም ከጥያቄ በኋላ ከእስር ተለቀዋል።
በሀገር ፍቅር በመነሳሳት ኮከብ አልባውን አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በቁመቱ ረጅም በሆነው የአዲስ አበባ ስታዲየም የመብራት ማማ ላይ የሰቀለው ወጣት ዋሲሁን አያኖ ይባላል።
ወጣቱ ስራው መምህርነት ሲሆን በኢትዮጵያ በህወሃት አገዛዝ የሚደርሰውን በደል ሲቃወም እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ።
በሰላማዊ መንገድ ባንዲራውን ከፍ ብሎ እንዲውለበልብ በማድረግ ሃሳቡን የገለጸው ወጣት ግን ከረጅሙ ማማ ላይ በፖሊስና በእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ መጨረሻው እስር ቤት ሆኗል።
ወጣት ዋሲሁን አያኖ በረጅሙ ማማ ላይ ከወጣ በኋላ ያውልውበልባቸው ከነበሩት የኢዮጵያ ሰንደቅ አላማዎች ጋር የተጻፈ ነገር ቢኖርም ከሩቁ ማንበብ አለመቻሉን በአቅራቢያው ሁኔታውን የተከታተሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ወጣት ዋሲሁን አያኖ ለእስር ከተዳረገ በኋላ የሰራው ወንጀል ምን እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም።
ይሁንና ወጣቱ በሰላምዊ መንገድ ተቃውሞውን የገለጸበት መንገድ ሕዝቡን ለአመጽ ሊገፋፋ ይችላል በሚል በአገዛዙ ስጋት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጠራው የወላይታ ተወላጆች ስብሰባ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙትና ግቢውን ጥሰው በመግባታቸው የታሰሩት ሁለቱ የዲሲ ግብረ ሃይል አባላት በፖሊስ ተይዘው ጥያቄ ከቀረበላቸው በኋላ ተለቀዋል።
በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲውለበለብ የነበረውን ባለኮከብ ባዲራ ለማውረድ የሞከረው የግብረ ሃይሉ አባል ሰንደቅ አላማው የታሰረበት ገመድ በመቆለፉ ማውረድ ሳይችል ቀርቷል።
በኋላ ላይም ከግቢው አልወጣም በማለቱ በፖሊስ ተይዞ ሲታሰር የግብረ ሃይሉ ሌላው አባልም ሁኔታውን ሲያስረዳ የጸጥታ ሰራተኛውን ነክተሃል ተብሎ ለመታሰር በቅቷል።
ይሁንና ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሁለቱም የዲሲ ግብረሃይል አባላት ከእስር መለቀቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።