ሚያዚያ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ 5ተኛ ተከሳሽ የሆነው ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) የፌዴራል ዐቃቤ-ህግ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ላቀረበው አቤቱታ ምላሽ የሚሰጥ የምሥክርነት ቃሉን ዛሬ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት አሰምቷል፡፡
የመኢዴፓ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነው ክንፈሚካኤል ደበበ ” በፍትህ ጋዜጣ ቅጽ 6 ቁጥር 183 ዓርብ ፣ ሚያዚያ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በገጽ 4 ላይ በእኔ ሥምና ፎቶ የተስተናገደው “ማቆሚያና ገደብ ያጣው የምስኪኗ እናቴ እንባ!” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሑፍ የኔ የግል እምነትና አመለካከት ነው፤ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጽሑፉን እንዲታተም ከመፍቀድ በስተቀር የእርሱ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የለበትም፤ በጽሑፉ የምጠየቅም ከሆነ ኃላፊነቱ የኔ ነው” በማለት ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም “ይህ የመጠየቅ ያለመጠየቅ ጉዳይ አንተን አይመለከትህም፣ የተጠየቅከውን ብቻ መልስ ስጥ” በሚል ገስፆት፣ “ለመሆኑ ጽሑፉ ከማረሚያ ቤት በምን ሁኔታ ነው የወጣው?” ሲል በአጽንኦት ላቀረበለት ጥያቄ አቶ አበበ ሲመልስ “ይሄን ጽሑፍ እዚህ ችሎት የተከሳሽነት ቃላችንን እንድንሰጥ የተጠየቅን ጊዜ ያዘጋጀሁት ሲሆን ነገር ግን በጊዜው የተከሳሽነት ቃላችሁን በቃል አቅርቡ በመባሉ በቤተሰቦቼ በኩል ወደ ፍትህ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ልኬዋለሁ” በማለት ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም- አምስተኛ ተከሳሽ ዐቃቤ-ህግ ተጨማሪ አቤቱታ ባቀረበበት ጽሑፍ ላይ ምላሹን ስለሰጠ ግራ ቀኙን አገናዝበን ውሳኔ ለመስጠት እንዲረዳን ዛሬ ተከሳሹ የሰጠው ቃል ቅጂ ወደ ጽሑፍ ተቀይሮ ለጽ/ቤት ቀደም ብሎ ይቅረብ በሚል ለሰኞ ሚያዚያ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኗል፡፡
በችሎቱ ላይ በርካታ የፍትህ ጋዜጣ አንባቢያን ከውስጥና ከውጭ የታደሙ ሲሆን፣ ከችሎት ውጪም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ከበው ሲያበረታቱ የደህንነት ሠራተኞችም አብረው ተጠግተው ሲሽሎከሎኩ እና ሰውን ሲቃኙት ተስተውለዋል፡፡
ችሎቱ መዝገቡን ማየት ሲጀምር የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ቅሬታ ያቀረበበት ጽሑፍ በእርግጥም በ5ተኛ ተከሳሽ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ስለመጻፉ ተከሳሹ ከማረሚያ ቤት መጥተው ለችሎት እንዲያስረዱ በመወሰኑ መሆኑን አውስቷል።
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ዛሬ ዓርብ ሚያዚያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ላይ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ከነጋድራስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሱራፌል ግርማ ጋር ቢሆንም የችሎቱ ትኩረት ሙሉ በሙሉ ፍትህ ጋዜጣና ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ላይ ነበር፡፡
የመንግስት የመገናኛ ብዙሀንና የኢህአዴግ ደጋፊ ድረገጾች በፍትህ ጋዜጣ ዘገባ ዙሪያ ተደጋጋሚ ትችቶችን ማቅረባቸው፣ ገዢው ፓርቲ ምን ያክል እየተጨናነቀ እንደመጣ ያሳያል በማለት አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አሳታሚ ተናግሯል። መንግስት ብዙ አፎች አሉት፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ዋነኛው አፉ ነው፣ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አፎች እያሉት በአንድ ጋዜጣ ተርበትብቷል፣ ይህ የሚያሳየው የእውነትን አሸናፊነት ነው ብሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአቶ አማረ አረጋዊ የሚመራው 4 አባላት ያሉት የአሳታሚዎች ኮሚቴ ከብርሃንና ሠላም የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትላንት ተነጋግሮ በጉዳዩ ላይ ለመመካከር ለሜይ 7/2012 ቀጠሮ ይዟል፡፡የማተሚያ ቤቱ ቀነ ገደብም እስከሚነጋገሩ ደረስ ተራዝሟል፡፡ይህም ሆኖ ግን በማተሚያ ቤቱ በኩል ሃሳባቸውን የመቀየር አዝማሚያ የለም ተብሏል፡፡ ብርሀንና ሰላም የጋዜጦችን ይዘት በመገምገም ለማተም ወይም ላለማተም የሚያስችለውን አዲስ ህግ ማውጣቱን ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል። የጋዜጦች አሳታሚዎችም ትናንት ተሰባስበው አዲሱን የማተሚያ ቤት ደንብ እንደሚቃወሙት አስታውቀዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide