ከ600 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ

(አራት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-ትእዛዙን የሰጠው የቦሌ ክፍለከተማ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ እስከ ማክሰኞ ቤታቸውን ለቀው ካልወጡ ፣ አፍራሽ ግብረሀይል በጉልበት እንደሚያፈርስባቸው አስታውቋል።

“በሶስት ቀናት ውስጥ የት እንሄዳለን?’ ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪዎች ፣በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚታየው የቤት ኪራይ መጨመር አስግቶናል ብለዋል። ሜዳ ላይ እንዃ እንዳንወድቅ ሜዳውም እየታረሰ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ባለስልጣናት በስልጣናቸው ደሀ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ ቦታዎቻቸውን እየወሰዱባቸው ነው። ነዋሪዎች እንደሚሉት አርሶአደሮች በጉልበት መሬታቸውን እየተቀሙ ለደነነት  ተዳርገዋል። መሬታቸውን ከተቀሙት አርሶ አደሮች መካከል በሰበታ ነዋሪ ከሆኑት አንዱ ሲናገሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት የአቶ ደምሴ ቡላ ባለቤት መሬታቸውን በጉልበት እንደነጠቁዋቸውና ክስ ሲመሰርቱም እንዳሳሰሩዋቸው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ቤት ሰርተው ይኖሩ ነበሩ ሰዎች ቤቶቻቸው ከፈረሱባቸው በሁዋላ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ይታወቃል።