በአዲስ አበባ የመሬት ማኔጅምንት እና ተዛማጅ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸውን አመራሮች ገለጹ፡፡

(አራት)ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አልፎ አልፎ አንዳንድ አመራሮች በአመለካከትም ሆነ በተግባር በሙስና ተዘፍቀው ተገኝተዋል ያለው የአስተዳደሩ ሰነድ፣ በከተማው ውስጥ ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታና ሕገወጥ ንግድ አሁንም አሳሳቢ ችግሮች ሆነው መቀጠላቸውን አትቷል፡፡

በትላንትናው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮችን ጠርቶ የመከረው ቢሮው ችግሮች በስፋት የመልካም አሰተዳደር እጦት መገለጫ እየሆኑ መምጣታቸውን የቢሮው ሃላፊ አቶ ሰለሞን ሃይላይ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በከፍተኛና በመካከለኛ አመራሮች ዙርያ ግምገማ አካሂዶ ትንታኔ የሰጠበት ሰነድ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

ከፍተኛ አመራሮች ሥራዎችን ጠበቅ አድርገው ከመሥራት ይልቅ ያዝ ለቀቅ እንደሚያደርጉ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በሥራ የሚሰላቹና በተወሰኑ ሥራዎች የሚረኩ፣ የጠባቂነት ዝንባሌ የሚታይባቸው መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩልም የፀረ ሙስና ወይም ኪራይ ሰብሳቢ እና ሕገወጥነት ትግል በማካሄድ በኩል ዳተኝነት ይታያል፡፡ አልፎ አልፎም አንዳንድ አመራሮች በአመለካከትም ሆነ በተግባር የችግሩ ሰለባ ሆነው መገኘታቸውን ሰነዱ ያብራራል፡፡ ሰነዱ በመቀጠል አንዳንድ አመራሮች እነዚህን ችግሮች ታግለው ከማስተካከልና ሥርዓት ከማስያዝ ይልቅ አይቶ እንዳላየ ያልፋሉ፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በአመራሮች መካከል የሚካሄደው የእርስ በእርስ ትግል ከአድርባይነት ያልፀዳ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፤›› ይላል ሰነዱ፡፡

አልፎ አልፎም በመርህ ላይ ተመሥርቶ ከመታገል ይልቅ በኔትወርክና በቡድንተኝነት መጠቃቃት በመካከለኛ አመራሮች አካባቢ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሰነዱ ትንታኔ አቅርቦ አመራሮቹን ወቅሷል፡፡

በመካከለኛ አመራሩም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ ሰነዱ ትንታኔውን ያቀርባል፡፡ መካከለኛ አመራሮች የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታና ሕገወጥ ንግድ በየአካባቢያቸው ሲስፋፉ አይተው እንዳላዩ የሚሆኑ አሉ ብሎአል፡፡

“አልፎ አልፎም በእነዚህ ጉዳዮች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ድርድር ያካሂዳሉ፣ ለሕገወጦች ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ይደለላሉ የሚለው ሰነዱ፣ በተግባር ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ መኖራቸውን ይዘረዝራል፡፡

እንደ ቢሮው ሃላፊ ገለፃ 40 ሄክታር መሬት፣ ሰዎች ከቦታው ሳይነሱ ፤ በምትኩም ሌላ ቦታ ሳይሰጣቸው በላያቸው ላይ ለኢንቨስትምንት ግንባታ ነፃ ያልሆነ መሬት ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡

ኅዳር 2004 ዓ.ም. የወጣው የሊዝ አዋጅ፣ መሬት በድርድር እንደማይሰጥ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የከተማው አስተዳደር፣ ለአገር ይበጃል ያለው ፕሮጀክት፣ የሚፈልገውን መሬት ለካቢኔ አቅርቦ ማስወሰን እንደሚችል ጨምሮ ደንግጓል፡፡ ከዚህ ውጭ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች በውስን ጨረታ እንዲሁም ለአልሚዎች በግልጽ ጨረታ ብቻ መሬት እንደሚቀርብ በአዋጅ መደንገጉ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየቀረቡ ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ በውስን ጨረታ ሊስተናገዱ የሚችሉ ፕሮጀክቶች፣ አገራዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተደርገው እንደሚታዩ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሊዝ አዋጅና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው መመርያ የሐሳብ ልዩነት እንዳላቸው የሚገልጹ የአስተዳደሩ መሬት ሥሪት ባለሙያዎች፣ ሥራቸውን በተረጋጋ መንፈስ መሥራት እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡