(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 14/2009)በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚመራው/ሕወሃት/ የሚመራው መንግስት ለ2010 በጀት ከ320 ቢሊየን ብር በላይ በፓርላማ ሲያጸድቅ የበጀት ጉድለቱ ከ1 መቶ ቢሊየን ብር በላይ ማለትም የበጀቱ አንድ ሶስተኛ መሆኑን አሳውቆ ነበር።
ይህንን ተከትሎም የአዲስ አበባ አስተዳደርና ሌሎች ከልሎችም በጀታቸውን ሲያጸድቁ የበጀት ጉድለታቸው የብዙዎቹ ከፍተኛ መሆኑም ነበር የተገለጸው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በነዋሪዎችና በተለይም በዝቅተኛ ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ የግብር ጫና መጣሉ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
የቀን ገቢ ግብር ግምት በመባል የሚታወቀው በገማች ኮሚቴና በካድሬዎች የሚሰራው ቀመር ፍትሃዊ ያልሆነና በአድሎ የሚሰራ መሆኑም ብዙዎችን ምሬት ውስጥ ነው የከተተው።
እናም ህብረተሰቡ የተጫነበትን ከፍተኛ ግብር በመቃወም በመንግስት ላይ ያለውን ምሬት በአደባባይ መግልጽ ጀምሯል።
]በኦሮሚያ አምቦ፣ጊንጪ፣ባኮና ነቀምት እንዲሁም በበርካታ የክልሉ ከተሞች የተጀመረው ተቃውሞ መደብሮችንና ሱቆችን በመዝጋት የተወሰነ አልነበረም።
በአንዳንድ አካባቢዎች መኪኖችን ማቃጠልና የትራንስፖርት አውታሮችን መዝጋትንም ይጨምራል።
በኦሮሚያ የተጀመረው ህዝባዊ አመጽ ወደ አማራ ክልልም እየተዛመተ ይገኛል ነው የተባለው።
ምንጮቻችን እንደገለጹት በአማራ ክልል ሸበል በረንታና ወረታ እንዲሁም በደሴና ወልዲያ ህዝቡ ተቃውሞውን ማሰማት ጀምሯል።
በሸበል በረንታ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው አካባቢው ጭር ሲል በወረታ ደግሞ ባጃጅ መቃጠሉ ተነግሯል።
በሰሜን ሸዋም በተለያዩ አካባቢዎች የአድማ ጥሪ ወረቀት ሲበተን ከነቀምት 48 ኪሎ ሜትር ረቀት ላይ በሚገኘው የጅማ አርጆ ወረዳ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተገድቧል።በቡራዩም ንግድ ቤቶች መዘጋታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በመላ ሀገሪቱ እየተዳረሰ ያለው ተቃውሞ ከግብር ጭማሪው ተቃውሞው ሌላ የአገዛዙ ስልጣን እንዲያከትም የሚጠይቅ መሆኑንም ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን ተቃውሞ በሐገሪቱ ያለው አገዛዝ ለመሸፋፈን ቢሞክርም በአንዳንድ ቦታዎች የታዩትን በማመን የማስተካከያ ርምጃ እንወስዳለን በማለት እየተማጸነ መሆኑን የኢሳት ምንጮች አመልክተዋል