መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከአመት በፊት የጀመሩትን ተቃውሞ በመቀጠል በአርብ የጁማ ጸሎት ላይ መንግስት ከደሀው ህዝብ በግብርና በተለያዩ መዋጮች ስም የሰበሰበውን ከ313 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አህባሽ የተባለውን ሀይማኖት ለማስፋፋት ማዋሉን አጥብቀው በመቃወም ገንዘቡ ለልማት እንዲውል ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ በአንዋር መስጊድ በተካሄደው ከፍተኛ ተቃውሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የታሰሩት ይፈቱ፣ በአገራችን ሰላም አጣን፣ ኢቲቪ አሸባሪ፣ መንግስት የለም ወይም፣ ህገመንግስት የለም ወይ፣ የሀሰት ክስ አይገዛንም፣ አህባሽ አይጫንብን ፣ ትግሉ ይቀጥላል፣ ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ ጥያቄያችን ይመለስ ፣ እኔም አቡበክር ነኝ፣ ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችንም አሰምተዋል።
ከተቃውሞው በሁዋላ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የኢህአዴግ ካድሬዎች አንዳንድ ሙስሊም ወጣቶችን ለመያዝ ሙከራ ቢያደርጉም፣ ወጣቶቹ በጋራ ሆነው በመቃወማቸው የተያዙትን ወጣቶች ለማስለቀቅ መቻላቸውን ዘጋቢያችን ከስፍራው ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን በአጋሮ ከተማም እንዲሁ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት የተቃወሙ ሲሆን፣ ከተቃውሞው በሁዋላ 4 ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ( )
በመላው አለም የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት የሚገኙ መሪዎቻቸውን በማሰብ የሚያደርጉት ተቃውሞ በቀላሉ የሚቆም አልሆነም። መንግስትም ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄው በራሱ ጊዜ ሊሞት ይችላል የሚል አማራጭ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ።