በአዲስ አበባ ከሚገኙ 26 የትራፊክ መብራቶች አገልግሎት የሚሰጠው አንዱ ብቻ ነው

መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ ከሚገኙ 26 የትራፊክ መብራቶች  ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ አለመሥራታቸው ፤  የትራፊክ መጨናነቅና የአደጋ መንስኤ መሆኑ ተዘገበ።

እንደ አድማስ ዘገባ የመብራቶቹ አለመሥራት ከዚህም ባሻገር  በትራፊክ ፖሊሶች ላይ ከአቅም በላይ የሆነ የስራ ጫና ፈጥሯል፡፡    ==

አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠሩት የከተማዋ የትራፊክ መብራቶች ሲበላሹ ጥገና ስለማይደረግላቸው ለበለጠ ብልሽት እየተዳረጉ ከጥቅም ውጪ እንደሆኑ የተናገሩ አሽከርካሪዎች፤ የትራፊክ መብራቶቹ በፍጥነት ታድሰው ወደ ሥራ ካልገቡ፣ አሁን የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅና የመኪና አደጋ ሊያባብስ እንደሚችል አስተንቅቀዋል፡፡

ከስታዲዬም መገናኛ ባለው መስመር የሚሰራው የታክሲ ሹፌር ዮሐንስ ጥጋቡ፤ ቀደም ሲል የለገሃሩን ሳይጨምር አምስት ቦታዎች ላይ የትራፊክ ማሳለጫ መብራቶች የነበሩ ቢሆንም አሁን አንዳቸውም እንደማይሠሩ ገልፆ ፤ በተለይ መስቀል አደባባይ እና እስጢፋኖስ ቤ/ክርስቲያን እንዲሁም ለም ሆቴል አካባቢ የመብራቶች አለመኖር ለመኪና አደጋ መከሰት ሰበብ ሲሆኑ መታዘቡን ይናገራል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ፤ የመብራቶቹ መበላሸት የስራ ጫና እንደፈጠረባቸውና ሌሎች የደንብ መተላለፎችን በትኩረት እንዳይከታተሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

“ቀኑን ሙሉ መብራት በሌላቸው ቦታዎች ተሽከርካሪዎችን እያስተናበሩ መዋል በራሱ ከፍተኛ ድካም አለው” ሲሉ ተናግረዋል – የትራፊክ ፖሊሱ፡፡

 

የመብራቶቹ መበላሸት በአባሎቻቸው ላይ የስራ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር አደጋን በማባባስም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉት የአዲስ አበባ ትራፊክ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው፤ ግንባታቸው በተጠናቀቁ የመዲናዋ መንገዶች ላይም የመብራት ተከላው በፍጥነት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አሣስበዋል።

በከተማዋ በ26 ቦታዎች የትራፊክ መብራቶች ቢኖሩም  በአሁን ሰአት  የሚሠራው ፖስታ ቤት አካባቢ ያለው አንዱ መብራት ብቻ እንደሆነ ካዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።