(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011)ከስራ ገበታቸው ተይዘው በግፍ የታሰሩትና በለውጡ ሳቢያ የተፈቱት አብራሪዎች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር ጠየቀ።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ “አዲሱ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዕጣ ፈንታ ያገባናል” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ለውጡን እንደሚደግፍና የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ለማጠናከር በሚሰሩ ስራዎች ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑንም አመልክቷል።
ሆኖም በግፍ ተይዘው በስቃይ ላይ የቆዩት የበረባ ባለሙያዎች እስከአሁን ወደ ስራ ገበታቸው አለመመለሳቸው እንዳሳሰባቸው አመልክቷል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ ከ25 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ለማዳከምና በዘረኝነት ለማዋቀር የተወሰደውን ርምጃ በቁጭት አስታውሷል።
በዚህም ሳቢያ ከ50 በላይ የበረራ ባለሙያዎችና ቁጥራቸው ያልታወቁ የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማስወገድ አየር ሃይሉን በማዳከምና ባለሙያዎቹን በማንገላታት የተፈጸሙ ድርጊቶቹንም በመግለጫው የዘረዘረው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር በወጣቶቹ አዲስ የበረራ ባለሙያዎች ላይ የተፈጸመውንም ድርጊት ጠቅሷል።
በዚህ ሰቆቃ ተቋዳሽ ነበሩ ሲል የዘረዘራቸው ወጣት የበረራ ባለሙያዎች የመቶ አለቃ በሃይሉ ገብሬ፣ የመቶ አለቃ አብዮት ማንጉዳይ፣ የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ የመቶ አለቃ ዳንኤል ግርማ፣ የመቶ አለቃ ገዛኸኝ ደረሰ እና የመቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ ከ4 እስከ 13 ዓመታት ታስረው መፈታታቸውን ገልጿል።
እነዚህ ባለሙያዎች ከእስር ቢፈቱም ወደ ስራቸው አለመመለሳቸው እንዳሳዘነው ማህበሩ ገልጿል።
ይልቁንም እነዚህ ወጣት የበረራ ባለሙያዎች ለስቃይ እንዲጋለጡ ያደረጉናተባባሪ የሆኑ ግለሰቦች አልፎ አልፎ በሃላፊነት ቦታ ላይ መገኘታቸውም እንዳሳዘነው ገልጿል።
መንግስት ወደ ስራቸው ይመልሳቸው ሲልም ጥሪውን አቅርቧል።