በአማራ ክልል ሶስት ቀበሌዎች ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥባቸው ነበር ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011) በአማራ ክልል ሶስት ቀበሌዎች ላለፉት አራት ዓመታት ከመንግስት መዋቅር ውጪ እንዲሆኑ ተደርገው ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጥባቸው እንደነበር የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ገለጹ።

ሃላፊው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በሰጡት መግለጫ የቅማንትን ጥያቄ አስታከው የተነሱ ሃይሎች ሶስቱን ቀበሌዎች ወታደራዊ ማሰልጠኛ አድርገው በክልሉ ሰሜን ክፍል በርካታ የሰው ህይወት የጠፋባቸውና ንብረት የወደመባቸውን ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው በስም ያልጠቀሱት አንድ አካል በቅማንት ጥያቄ ስም ክልሉን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ይታያል ብለዋል።

የቅማንት ኮሚቴ በሚል ራሳቸውን የሰየሙ አካላት በበኩላቸው የአማራ ክልል ባለስልጣናት ለፍርድ ይቅረቡልን ሲሉ በደብዳቤ ጠይቀዋል።

ዛሬም በአካባቢው ውጥረት ነግሷል። ሰሞኑን የበረታው ግጭት ቀጥሎ ከሁለቱም ወገኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል።

በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል። ሶስት ሰዎች ተገድለዋል። የአማራ ክልል የሰላም ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መገለጫም በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ግጭት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ላይ ላዩን የቅማንት የአስተዳደር ጥያቄ የሚመስል በዋናነት ግን በአካባቢው በሚፈጥር ትርምስና ሁከት የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው ያሰሉ ሌሎች ሃይሎች በመሳሪያና በገንዘብ የሚደግፉት ጥቃት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአስተዳደር ጥያቄው በህጋዊ መንገድ ከተመለሰና ቅማንት ራሱን የሚያስተዳድርበት መዋቅር ከተፈጠረ በኋላ ጥቃቱ የቀጠለው ቀድሞውኑ ጥቃቱ የሌሎች ወገኖች ፍላጎት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ገልጸዋል።

እነዚህ በስም ያልተጠቀሱ ወገኖች አካባቢውን ለማወክ ሦስት ቀበሌዎችን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ በማድረግ ላለፉት አራት ዓመታት የወታራዊ ማሰልጠኛ ማድረጋቸውን ነው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የሚገልጹት።

እነዚህ ከጀርባ ቀውሱን ያቀጣጥሉታል በሚል የሚገለጹ ሃይሎችን በተመለከተም የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አሰማህኝ አስረስ የግጭቶቹ ስፓንሰር አድራጊዎች ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል።

እሳቸውም ማንነታቸውን በግልጽ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል። በተለይም በጭልጋ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዛሬ ከስፍራው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ወደ ሱዳን በሚወስደው ዋና መስመር ላይ ባለፉት አራት ዓመታት ዘረፋና ጠለፋ ሲካሄድ እንደነበረ የሚገልጹት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ሰሞኑን ይህ ድርጊት በስፋት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በቁጥር ያልገለጹት ሰው በእነዚህ ሃይሎች ተጠልፎ የት እንደሚገኝ እንደማይታወቅም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ይህን ቀውስ እልባት ለመስጠት ርምጃ መውሰድ ጀምሯልም ነው የሚሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ።

የቅማንት የማንነት ሆነ የአስተዳደር ጥይቄ ምላሽ በተሰጠበት ሁኔታ ችግሩ ሊቀጥል የቻለው ከቀውሱ ባሻገር ዓላማ ሰንቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መሆናቸውን በተመለከተ ኢሳት ባደረገው ማጣራት የህወሃት ቡድን የቅማንትን ጥያቄ በስውር ባለቤትነት እንደሚመራው ለመረዳት ችሏል።

ለዚህም በመቀሌ ጽሕፈት ቤት ከመክፈት አንስቶ የጦር መሳሪያ በስውር በማስገባት ቀውሱን እያባባሰው እንዳለም የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

በህወሃት የኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ድርጅት ተሽከርካሪዎች በመሳሪያ ዝውውር ውስጥ እጃቸውን ማስገባታቸውም ታውቋል።

ከዚህ አንጻር ሱር ኮንስትራክሽን እንደሚገኝበት ነው የመረጃ ምንጮች የሚጠቁሙት። በቅርቡ የቅማንት ኮሚቴ ነን የሚሉ ወገኖች ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ በ12 የአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ ክስ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።