ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ከባድ ተሸካሚ መስመር መዘረፍ
በኃላ መብራት ባጣችው በድሬዳዋ ከተማ የሸቀጦች ዋጋ በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎች አረጋገጡ፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከምሸቱ አንድ ሰዓት አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ ከዚያ በኃላ
በከተማዋ የመጠጥ ውሃ መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአንድ ብርጭቆ የመጠጥ
ውሃ ዋጋ 0.25 ሳንቲም፣ የ20 ሊትር ጄሪካን ውሃ ዋጋ 6 ብር፣ለትራንስፖርት ደግሞ 10 ብር እየተጠየቀበት
መሆኑን፤ በዚህ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ
ጠቁመዋል፡፡
በየሆቴሉ በምግብ ወቅት እንኳን ለእጅ መታጠቢያ ውሃ ማግኘት አለመቻሉን፣ገላን በውሃ መታጠብ ቅንጦት
እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ከሁኔታው ጋር ተያይዞ እንደኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሸታዎች እንዳይከሰት ሥጋት
መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ የተተኪ ጄኔሬተር ኃይል አማራጭ እንኳን ባለመኖሩ ነዋሪዎች በፈረቃ እንኳን ኃይል እንዳያገኙ ሆኗል
ያሉት ነዋሪዎቹ እህል አስፈጭቶ ለመብላት ጨርሶ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋርም ተያይዞ 2 ብር ከ50 እና 3 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ደረቅ እንጀራ በአንድ ሳምንት ጊዜ በእጥፍ
አድጎ 6 ብር መግባቱን፣ዳቦ በእንጨት ብቻ ስለሚጋገር የዳቦ እጥረት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሸን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መስመሩ መቼ ተጠግኖ እንደሚጠናቀቅ እንኳን እንደማያውቁ
እየተናገሩ መሆናቸው ነዋሪውን ይበልጥ ማስደንገጡን አስረድተዋል፡፡
በትላንት የፓርላማ ውሎ መንግስት ለድሬዳዋ የሃይል መቋረጥ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ የተጠየቀ ሲሆን በመድረኩ ላይ የተገኙት ጠ/ሚኒስትር ኃለማርያም ደሳለኝ ችግሩ ከዘረፋ ጋር ተያይዞ መፈጠሩንና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረግ መሆኑን ከመናገር ውጪ እስከመቼ ተጠግኖ እንደሚያልቅ ፍንጭ አልሰጡም፡፡ ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ችግሩ በነገው እለት ይፈታል በማለት ገልጻል