ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአባይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት እቅድ እንደሚያሳየው ግድቡ ሲጠናቀቅ 1600 ኪሎሜትር ስኩየር መሬት የሚሸፍን ውሃ የሚተኛበት ሲሆን፣ የዚህ መሬት አካል 90 በመቶው በደን የተሸፈነነ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተሻለ የደን
ሽፋን አለው የሚባለው ግድቡ የሚሰራበት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቢሆንም፣ ከ200 ኪሎ ሜትር ያላነሰ ስፋት ያለው የክልሉ ደን በፍጥነት እየተጨፈጨፈ ነው።
እጅግ የሚያሳዝነው ይላሉ አካባቢውን ለመግብኘት የሄዱ ታዛቢዎች፣ ደኖችን እየመነጠሩ የሚሸጡት ከአንድ አካባቢ የተሰባሰቡ የህዝባዊ ወያን ሃርነት ትግራይ ደጋፊ ባለሀብቶች ናቸው። ደኑን መንጥሮ የመሸጥ ሃላፊነት የተሰጣቸው እነዚህ ታማኝ የህወሃት ነጋዴ አባላት፣ ከቤንሻንጉልና ከተለያዩ አካባቢዎች የሰበሰቡዋቸውን
የጉልበት ሰራተኞች አነስተኛ በሆነ ክፍያ እያሰሩ ለራሳቸው መሰብሰባቸው ነው። አሰሪዎቹ ታክስ አይከፍሉም፣ እጅግ አነስተኛ ክፍያ ከሚከፈላቸው ሰራተኞች ላይ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ እያሉ የሚሰበስቡትን ገንዘብም ወደ ኪሳቸው ያደርጉታል ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ።
ነጋዴዎቹ ከሰል በማክሰል ወደ ሱዳንና አዲስ አበባ እያመጡ ከመሸጥ በተጨማሪ፣ በትላልቅ መኪኖች እንጨቶችን ወደ ከተሞች በመላክ እየሸጡ በወር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየዘረፉ ነው።
አካባቢውን በቅርብ ጎብኝቶ የመጣ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ሰው ሲናገር ደግሞ ፣ አሰሪዎቹ እንጨት ጭነው ወደ መሃል አገር በሚሄዱበት ወቅት ዛፎችን የሚቆርጡ ሰራተኞች በየጫካው እየተረሱ ችግር እየደረሰባቸው ነው።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ከደን ምንጠራው በተጨማሪ በግድቡ ዙሪያ ከባድ እቃዎችን ከማቅረብ ጀምሮ ሻሂ እስከመሸጥ ያሉ ስራዎችን የህወሃት ታማኞች መቆጣጠራቸው እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።