ከአርማና ሰንደቃላማ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ተቀሰቀሰ
( ኢሳት ዜና መስከረም 03 ቀን 2011 ዓ/ም ) የፊታችን ቅዳሜ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትን በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል በሚካሄደው ዝግጅት ላይ የኦነግን አርማ ለመስቀል እና መንገዶችንና አጥሮችን በኦነግ አርማ ለመቀባት አደባባይ የወጡ ወጣቶች፣ ድርጊቱን ከሚቃወሙ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ተጋጭተዋል። የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ግጭቱ እንዳይባባስ የማረጋጋት ስራ ሲሰሩ የዋሉ ሲሆን፣ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማልን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወጣቶች ካላስፈላጊ ግጭት እንዲርቁ መክረዋል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ ማንኛውም ሰው ይወክለኛል ያለውን አርማ ይዞ መውጣት መብቱ እንደሆነና በዚህ ሰበብ የሚደርሰው ጉዳት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲገልጹ፣ የፖሊስ ኮሚሽነሩም መንገዶች ላይ ቀለም መቀባት ትክክል አለመሆኑን ገልጸው ማስቆማቸውን ተናግረዋል። የኦነግ መሪዎችን የሚቀበለው ኮሚቴ በበኩሉ የድርጅቱ አርማውን መሰቀሉ ትክክል ቢሆንም፣ መንገዶችን መቀባት ትክክል አለመሆኑን ገልጿል። የቄሮ አባላት ከግጭት እንዲርቁም መልዕክት አስተላልፏል።
አርበኞች ግንቦት7 ባወጣው መግለጫም፣ ማናቸውም ቡድን ወይም ሃይል ይወክለኛል ያለውን ባንዲራ/ምልክት ማውለብለብ ይችላል ብሎአል። ግንባሩ “በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ወደ አገራቸዉ ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በጎዳናዎች ላይ የሰቀሉትን የድርጅታቸውን ባንዲራ እናወርዳለን በሚሉና መውረድ የለበትም በሚሉ ሀይሎች መካከል የተነሳዉአግባብ የለሽ ግጭት ንቅናቄያችን የሚታገልለትን የዲሞክራሲ መርህ የሚጻረር ተግባር ከመሆኑም
በላይ በአገራችን የፈነጠቀውን የመቻቻል ፖለቲካ ከጅምሩ የሚያደበዝዝ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7 ድርጊቱን በጽኑ እያወገዘ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች ቢኖሩ ከዚህ አይነቱ ትርጉም የለሽና ፀረ-ዲሞክራሲ የሆነ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲታቀቡ” አሳስባለሁ ብሎአል።
በሌላ በኩል ማንነታቸው ያልታወቁ አንዳንድ የቀበሌ ሰራተኞች ግጭቱ እንዲባባስ ውስጥ ለውስጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።