ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከ60 ሺ በላይ ሰዎች ሰዎች ሲፈናቀሉ የማቾችም ቁጥር እያሻቀበ ነው
( ኢሳት ዜና መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ/ም ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሺ ዞን አመራሮችና በኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት መካከል ቀደም ብለው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ክልሉ ለመመለስ ድርድር አድርገው ሲመለሱ የተገደሉ 4 የቤንሻንጉል ጉሙዝ ባለስልጣናትን መገደል ተከትሎ በተወሰደ የአጸፋ እርምጃ በክልሉ የሚኖሩ ከ60 ሺ በላይ የኦሮሞ፣ አማራና ሌሎችም ብሄሮች ተወላጆች ተፈናቅለዋል። እስካሁን ድረስ ከ12 ያላነሱ ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ዜጎችም ቆስለዋል። ለባለስልጣኖች ግድያ የኦሮምያ ክልል የኦነግ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ሲያደርግ፣ ኦነግ በበኩሉ አስተባብሏል።
በበሎይ ጅጋንፎይ ወረዳ፣ በተንካራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ሲቃጠሉ ከ4 ያላነሱ ሰዎች ህይወት አልፏል። በምስራቅ ወለጋ የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር እስከ 60 ሺ የሚደርስ ሲሆን፣ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ100 ሺ ሊያልፍ እንደሚችል የአካባቢው ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳስነበቡት፣ ግጭቱ በመንዲ ከተማ የሁለቱ ክልል ባለስልጣናት ውይይት አድርገው ሲመለሱ ፣ ቢላ በተባለ ቦታ ላይ በኦነግ_ስም የታጠቁ ወታደሮች ባለስልጣናቱን በያዙት መኪና ላይ ተኩስ ከፍተው የከማሲ ዞን አስተዳዳሪውን ጨምሮ 4 ሰዎችን በመግደላቸው የተፈጠረ ነው። በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂዎችን መንግስት እስካሁን ለምን ትጥቅ እንዳላስፈታቸው የታወቀ ነገር የለም። አስመራ የነበረው ዋናው የኦነግ አመራር በሰላማዊ ትግል ለመታገል ወስኖ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል። በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች አዲስ አበባ ከሚገኘው የኦነግ አመራር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ኦነግ ግን እንዲህ አይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ታጣቂዎች እንደሌሉት በመግለጽ ላይ ነው።