የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዛት ያላቸው ነባር አመራሮቻቸውን አሰናበቱ

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዛት ያላቸው ነባር አመራሮቻቸውን አሰናበቱ
( ኢሳት ዜና መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ/ም ) ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ያሉት የቀድሞው ብአዴን በአዲሱ ስያሜ የአማራ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ አዲፓ፣ የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያ ፓርቲ እና ህወሃት በርካታ ነባር አመራሮቻቸውን አሰናብተዋል።
ደኢህዴን የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ 23 ሰዎችን ሲያሰናብት፣ ከታዋቂዎቹ መካከል ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ሬድዋን ሁሴንና ሽፈራው ተክለማርያምን አሰናብቷል። ህወሃት በበኩሉ የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱን ጨምሮ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ሚካኤል አብረሃና አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይን ጨምሮ 12 ሰዎችን ከድርጅቱ አሰናብቷል። የአማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ በበኩሉ ከበደ ጫኔ፣ ፍሬህይወት አያሌው፣ ጌታቸው አምባዬን አሰናብቷል።
ህወሃት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ሊቀመንበር እንዲሁም ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚያብሄር፣ ም/ሊ ቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ሲወስን ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አለም ገብረዋህድ፣ አቶ አስመለሽ ወልደስላሴ፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስ አለምባሌማ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው ተመርጠዋል። እነዚህ ሰዎች ድርጅቱን ወክለው በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ አስታውቋል። በወንጀል ይፈለጋሉ የሚባሉት የቀድሞው የደህንነት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው አሰፋ በስራ አስፈጻሚነታቸው በአዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የሚገኙ ይሁኑ አይሁኑ የታወቀ ነገር የለም። ከዶ/ር አብርሃም ተከስተና ከወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በስተቀር ህወሃት የመረጣቸው የስራ አስፈጻሚ አባላት በሙሉ በዶ/ር አብይ አህመድ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ በመሆናቸው የኢህአዴግ የሃዋሳው ጉባኤ ብዙ ፍትጊያዎችን ሊያስተናግድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። የአማራ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ( አዴፓ ) የህወሃት ወኪል ተደርገው የሚቆጠሩትን ፍሬህይወት አያሌውን፣ ከበደ ጫኔንና ጌታቸው አምባዬን ከድርጅት ሲያሰናብት፣ አለምነው መኮንንን በትምህርት ሰበብ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዳይገባ እንዲሁም አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንን በስራ ስም በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዳይመረጡ በማድረግ፣ በጉባኤው ላይ ህወሃትን ሊደግፉ ይችላሉ ያላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ አስወግዷል። ደኢህዴንም እንዲሁ የህወሃት ደጋፊ ናቸው የሚባሉትን ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ሬድዋን ሁሴንና ሽፈራው ተክለማርያምን ቀንሷል።
አዴፓ ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ ያቀረባቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ጉባኤተኛው መልቀቂያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ በአመራርነት እንዲቀጥሉ ወስኗል።