ሰኔ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በቁጫ ወረዳ በቅርቡ ከተነሳው የመልካም አስተዳደር ፣ የማንነትና የፍትህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፍትህ አጥተው ያለፉትን ስምንት ወራት በእስር ቤት ካሳለፉ ትመካከል የ14 የቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪ የሆኑት የ39 ዓመቱ አቶ ሻልሼሸዋ ከሞቱና የሌሎችም እስረኞች ህይወት አደጋ ላይ በመውደቁ እንዲሁም በአካባቢው ድጋሜ ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት በመፍጠሩ 4 የአገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን ለፌደራሉ መንግስት በድጋሜ ለማመልከት ወደ አዲስ አበባ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል።
ሁለት ሴቶችና 2 ወንዶች የሚይዘው የአገር ሽማግሌዎች ቡድን በአካባቢው ስላለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በእስር ቤት ውስጥ ስለሚፈጸመው ግፍ ለመንግስት ባለስልጣናት የማሰማት እቅድ አለው።
ከዚህ ቀደም በህዝብ ተወክለው ጉዳያቸውን ለጠ/ሚንስትሩ ቢሮ ሲያቀርቡ የነበሩ የአገር ሽማግሌዎች አብዛኞቹ መታሰራቸው ይታወቃል።
300 ዎቹእስረኞች በአርባምንጭ እስር ቤት በህክምና አድሎአዊ በሆነ አያያዝ ከፍተኛ የሆነ መጎሳቆል እየደረሰባቸው መሆኑን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።