ከቀደምት የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት መካከል አንዱ የሆነው ይምርሃነ ክርስቶስ በመፈራረስ አደጋ ላይ ነው፡፡

ሰኔ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ከ1 ሺ 076 እስከ 1 ሺ 116 ዓ.ም በቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የተገነቡት እነኚህ ህንፃዎች በዓለምና በኢትዮጽያ ለጎብኝዎች ፣ ለትምህርትና ለጥናት የሚውሉ ቁምነገሮች የሞሉባቸው በመሆኑ ከአደጋ ለማውጣት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው  ይገባል ሲሉ የቤተክርሲቲያኑ አባቶች ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ለመንግስት ቢያቀርቡም   ምላሽ ማጣታቸውን የሚናገሩት አባቶች ፣ ሃዘናቸው ቅርሶችን ለመጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ ባልተወጣ መንግስት ላይ ነው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

የደብረሰሂን ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባወልደቂርቆስ ገብረ ስላሴ በዋሻ ውስጥ ከተገነቡት ሁለቱ ህንጻዎች መሰነጣጠቅና ከዋሻው በተናደ ድንጋይ የመደርመስ አደጋ ስለገጠማቸው አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ይምርሃነን ወደነበረበት ለመመለስ አስቸኳይ ጥረት ካልተደረገ ለዘልአለሙ ሊጠፋ እንደሚችል እስተዳዳሪው አስጠንቅቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዎሎጅና የቅርስ አስተዳድር ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር አለምሰገድ በልዳዶስ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉዳታቸው እየጨመረ የመጣው ሁለቱ ህንፃዎች በውሰጣቸው ያሉት ስዕሎች ፅሁፎችና ሌሎች ቅርሶችን በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት ለመመለስ እንክብካቤ ሰለሚያስፈልጋቸው  ወደ ነበሩበት መመለስ መጠገንና መጠበቅ ወይም ለዘላለሙ ማጣት በሚል መርህ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይምርሀነ ክርስቶስ ከአዲስ አበባ በ700 ከላሊበላ ደግሞ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት 80 ዓመታት ቀድሞ  በዋሻ  ውስጥ የተሰራ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዋሻው ውስጥ የንጉስ ቤተ መንግስትና ቤተክርስቲያኑ በአራት ሜትር ተራርቀው ይገኛሉ፡፡ቤተ መንግስቱም እንደ ቤተክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥበት መቆየቱን የደብረ ሰሂን ይምርሃነ ክርስቶስ አስተዳዳሪ አባ ወልደቂርቆስ ገብረስላሴ ገልፀዋል ፡፡

በሀይማኖት አባቶች የቀረበውን አስተያየት በመያዝ የባህልና ቱሪዝም ባለስልጣኖችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።