መድረክ የግብጽን ጥቃት በመከላከያ ብቻ እንመለክታለን ማለት ጊዜው ያለፈበት ስትራቴጂ ነው አለ

ሰኔ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክ  በአባይ ወንዝ መጠቀም ተፈጥሮአዊና ህጋዊ መብታችን ነው በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ፣ አባይንና ሌሎችን ወንዞቻችን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀም ብቸኛውና ዘላቂ መፍትሄ ቢሆንም በግብጽ በኩል ዝግጅትነት ባለመኖሩ፣ ችግሩን በብቃትና በአስተማማኝ መንገድ ለመመከት መፍትሄው አገራዊ መግባባት ነው ብሎአል።

ከውጭ የሚቃጣብንን ጥቃት በመድፍ በታንክና በሌሎች የጦር መሳሪያዎች ብቻ እንመክታለን ብሎ ማሰብ የተሳሳተና ጊዜው ያለፈበት አቅጣጫ ነው የሚለው መድረክ ፣ አስተማማኝ የአገር መከላከልና ደህንነት እውን ሊሆን የሚችለው በመንግስት፣ በዜጎች፣ በማህበረሰብና በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መግባባት ሲፈጠር ብቻ ነው ሲል አስታውቋል።

ገዢው ፓርቲ የአገርን ጉዳይ ከስልጣን ባሻገር መመልከት እንዳለበትና ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ጥልቅ ውይይቶችን እንዲያደርግ ጠይቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድነት ፓርቲ የ1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻውን ጀምሯል።

ለጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በሚላከው በዚሁ የፊርማ ማሰባሰቢያ ሰነድ ላይ ” የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ የጸረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ፣ በገጠርና በከተማ ህዝብን ማፈናቀል እንዲቆም፣ ለስራ አጥነትና ለኑሮ ውድነቱ መፍትሄ እንዲፈለግ ፣ በንግድ በኩል ፍትሀዊ ውድድር የሚፈጠርበት ሁኔታ እንዲመቻችና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና የውይይት እና የእቅር ሂደት እንዲጀመር  ይጠይቃል።