“ኦነግ አገሪቱን መምራት አለበት” ያሉ ሃይሎች የሰኔ 16ቱን የግድያ ሙከራ እንዳቀናበሩት አቃቢ ህግ ገለጸ
( ኢሳት ዜና መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ/ም ) ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ለአዲስ አበባ ህዝብ ንግግር ካደረጉ በሁዋላ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አቀነባበረዋል የተባሉ አምስት ግለሰቦች መስከረም 18 ቀን 2010 ዓም በልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት የሽብርተኝነት ክስ ሲመሰረትባቸው እንደተገለጸው፣ የግድያው አቀናባሪዎች አገሪቱ ቀድሞ በተመሰረተው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ( ኦነግ ) መመራት አለባት የሚል እምነት ነበራቸው። ተከሳሾቹ በዶ/ር አብይ የሚመራ መንግስት መኖር እንደሌለበት እንደሚያምኑ እንዲሁም “ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ብለው በማመናቸው ለግድያ መነሳሳታቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል።
ዶ/ር አብይ በህዝብ ስም የራሳቸውን ዓላማ እንጅ የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት የማያስፈጽሙ በመሆናቸው ተጠርጣሪዎች ጥቃቱን ለመፈጸም መነሳሳታቸቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል። የጥቃቱ ዋና አላማም ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን መግደል እንደነበር በክሱ ተመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ጌቱ ግርማ፣ አብርሃኑ ጃፋር፣ ጥላሁን ጌታቸው፣ ባህሩ ቶሎሳና ደሳለኝ ተስፋዬ የተባሉት ሲሆኑ፣ የጥቃቱ ዋና አቀናባሪ ደግሞ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የምትገኝ ገነት ታምሩ ወይም ቶለሺ ታምሩ የምትባል ሰው መሆኗን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
የአቃቢ ህጉን ክስ ተከትሎ አዲስ አበባ የሚገኘው የኦነግ አመራር እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ከተደረገው ሙከራ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን በማስነሳት የአብይ መንግስት የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እንደሚደረጉ መንግስት ሲገልጽ ቆይቷል።
በመስቀል አደባባይ ላይ በደረሰው ፍንዳታ 2 ሰዎች ተገድለው ከ150 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።