ኦነግ በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ የሚካሄደውን ጦርነት ህዝቡ እንዲያከሽፈው ጠየቀ
ድርጅቱ አቶ ለማንና ዶ/ር አብይንም አውግዟል
(ኢሳት ዜና ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ/ም) በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ባወጣው መግለጫ በቄለም ወለጋ ውስጥ “ ለምን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንቅስቃሴን ትደግፋላችሁ?” በማለት የጦር ሃይሉ ግዳጅ ወስዶ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ዘመቻው በኦሮምያ ክልል መስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ትእዛዝና እውቅና እንዲሁም በጄኔራል ገብሬ ዲላና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ቀጥተኛ አዝማችነት የሚመራው ነው ያለው ኦነግ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምስራቅ ኦሮምያ በኩል በሶማሌ ልዩ ሃይል በኦሮሞ ሀዝብ ላይ እየተካሄ ያለው ጦርነት በኢደስ መልክ ተጠናክሮ በመቀጠል እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በባቢሌና ጭናክሰን አካባቢዎች ህዝቡንና ከብቶችን በእሳት ማጋየት ሲደርስ በኦሮምያ ክልላዊ መንግስትም ይሁን በኦፒዲዮ በኩል እስካሁን ድረስ የመከላከል እርምጃ አልተወሰደም ሲል ክስ አቅርቧል።
የለማ መገርሳ አስተዳደርና ኦፒዲዮ በአንድ በኩል ስለለውጥና ተሃድሶ እያወራና ህወሃትን የሚኮንኑ መስለው ወደ ኦሮም ህዝብ እየቀረቡ በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በግልጽ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲያካሂዱ ለነበሩት እንደነጄኔራል ገብሬ ዲላ ሙሉ ስልጣን ሰጥተው በኦሮሞ ህዝብ ላይ እያሰማሩ ነው የሚለው ኦነግ፣ ዛሬ በተሃድሶ ለውጥ ስም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትንም ሆነ የፌደራሉን መንግስት የሚመሩት ግለሰቦች ወደ ስልጣን እንደሚጡ የረዳቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ወታደራዊ ሃይሉ፣ ቄሮ ቢሉስማ ኦሮሞና የኦሮሞ ልጆች ባጠቃላይ ከምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ በጋራ ለነጻነታቸው ሲሉ የከፈሉት መስዋትነት መሆኑ ማንም የማይክደው እውነታ ሆኖ ሳለ፣ እነዚህ ሰዎች ለኦሮሞ ህዝብ ከፍተኛ ጠላታዊ ስራ መስራታቸውን መቀጠላቸው በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው ብሎአል።
ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ይህን ዘመቻ እንዲጋፈጥ ጥሪ አቅርቧል።
የዶ/ር አብይ መንግስት ኦነግን፣ አርበኞች ግንቦት 7 እና ኦብነግን ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙ ይታወቃል። ኦነግ ከምንግስት ጋር ለመነጋገር ቃል በገባ በሳምንት ውስጥ የጦርነት አዋጅ ማወጁ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።