ያኮረፉ የኦህዴድ አባላት ለውጡን ለመቀልበስ ከሚንቀሳቀሱት ሃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ምንጮች ተናገሩ

ያኮረፉ የኦህዴድ አባላት ለውጡን ለመቀልበስ ከሚንቀሳቀሱት ሃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ምንጮች ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ/ም) ኦህዴድ ግጭት በመፍጠር፣በሙስናና በህዝቡ ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ያባረራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አባላች፣ የለውጡን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ እየሞሩ ካሉ ሃይሎች ጋር አብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። እነዚህ የተባረሩ የኦህዴድ አባላት የለማ እና የአብይን መሪነት ከሚቃወሙ ሃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር እንዲሁም ለውጡን ለመቀልበስ ከሚሰሩ የህወሃት እና አንዳንድ የብአዴን ነባር አመራሮች ጋር በመወገን የለውጡ እንቅስቃሴ እንዳያስካ እየተሯሯጡ ነው።
በደዴሳ የለማ ደጋፊ ተደርገው የሚቆጠሩ የኦህዴድ አባላት፣ ከስልጣን በተቀነሱ አባላት ሲሰደቡና ስልጣን ልቀቁ እየተባሉ ሲወገዙ እንደነበር ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
አብዛኞቹ በስልጣን ላይ እያሉ የዘረፉትን ገንዘብ በመጠቀም እና ከህወሃትና ለውጡን ለማደናቀፍ ከሚፈልጉት ሌሎች ሃይሎች ጋር በመተባበር እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ፣ ለውጡን ለሚደግፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላም የሚሰጥ አልሆነም። በነቀምት ከተማ ባለፉት 3 ቀናት ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ መታየቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከግጭቶች ጀርባ ያኮረፉ የኦህዴድ አባላትና የህወሃት ሰዎች እንዳሉበት ይናገራሉ።
የለማ አስተዳደር ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ቢሆንም፣ ለጊዜው የሰላም አማራጭን ለመጠቀም መምረጡ ፣ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩት ሃይሎች እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ እድል እንደከፈተላቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል።