ግንቦት ፲፩ (አስራ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት በላከው መግለጫ የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ የኦሮሞ ገበሬዎችን የአለአግባብ መፈናቀላቸውን በመቃወም የተደረገ በመሆኑ መላው ህዝብ ከጎናቸው ቆሞ ሊደግፋቸው ይገባል ብሎአል።
ገዢው ፓርቲ አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር እያጋጨ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት ዞሮ ዞሮ አገሪቱን የሚጎዳ በመሆኑ፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርቧል።
ገዢው ሃይል ታሪካዊውን የዋልድባን ገዳም ለስኳር ልማት በሚል ማፍረሱ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ ላይ የተካሄደ ዘመቻ መሆኑን እንዲሁም በጋምቤላ ህዝቡን በማፈናቀል መሬቱን ለውጭ ባለሃብቶች የመቸብቸቡ ሂደት አደገኛ እና ሊወገዝ እንደሚገባው ገልጿል። የኦሮሞ አርሶአደሮችን በማፈናቀል የሚወሰደው መሬትም በተመሳሳይ መልኩ ለባለሃብቶች ለመቸብቸብ የታቀደ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊቃወሙት ይገባል ብሎአል።
በአዲሱ የአዲስ አበባ መሪ ካርታ የተነሳ የሚፈናቀሉት ገበሬዎችን ለመታደግ የተጀመረው ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጸው ድርጅቱ፣ ኢትዮጵያውያን በብሄር፣ አካባቢ ወይም ሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በጋራ ሊነሱ ይገባል ብሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ በአምቦና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ላይ የተወሰደውን የግድያ እርምጃ በማውገዝ ከትናንት በስትያ በጀርመን ሙኒክ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል።
በሌላ ዜና ደግሞ ግንቦት11 ቀን 2006 ዓም ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ገንዘብ ለመሰብሰብ በተጠራው ስብሰባ ላይ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን እየተጠሩ አዳራሹን እንዲለቁ መገደዳቸውን ተከትሎ ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ታውቋል።
ኢትዮጵያውያኑ በዜግነታችን ስብሰባውን የመሳተፍ መብት አለን ቢሉም የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ግን ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ከአዳራሹ እንዲወጡ የተደረጉት ኢትዮጵያውያን በቅርቡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በመያዝ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና የሰብአዊ መብት ታጋዮችን ፎቶዎች በመያዝ ተቃውሞ አሰምተዋል።