ኦብነግ በምርጫ እሳተፋለሁ አለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2011) ከመንግስት ጋር በመደራደር የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ ሃገር ቤት የገባው  የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ / በምርጫ በመሳተፍ ሰላማዊ ትግሉን በይፋ እንደሚቀላቀል አስታወቀ።

ሆኖም ሃገሪቱ ላይ ሰላምና መረጋጋት ሳይፈጠር ምርጫ መካሄዱን እንደማይደግፈው የግንባሩ ቃለአቀባይ ገልጸዋል።

የኦብነግ የውጭ ጉዳይ ሃላፊና ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ከመንግስት ጎን ሆኖ ለመስራት ኦብነግ በሙሉ ሃይሉ ተዘጋጅቷል።

ከ40 ዓመታት በላይ ብረት አንስቶ ሲታገል የነበረው ኦብነግ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ለውጥ የድርሻውን ለማበረከት መዘጋጀቱን አቶ ሀሰን ገልጸዋል።

ግጭቶችን በመለኮስና በማቀጣጠል እጃቸውን ያስገቡ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

ኦጋዴንን ነጻ ለማውጣት ብረት ያነሳው በ1984 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነበር።

ባለፉት አርባ አመታት የነፍጥ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ በ2007 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በቻይና የነዳጅ አውጭ ኩባንያ ላይ በወሰደው የማጥቃት ርምጃ ዘጠኝ ቻይናውያንን ጨምሮ 74 ሰዎችን መግደሉ በዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጎታል።

ግንባሩ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የመከላከያና የሚሊሺያ ሃይል ላይ ወታደራዊ ድል እንደተቀዳጀ ሲገለጽ ቆይቷል።

ከህወሃት አገዛዝ ጋር አያሌ ድርድሮችን ቢያደርግም አንዱም የሰላም ንግግር ግንባሩን ትጥቅ አስፈትቶ ወደሃገር የሚያስገባው አልሆነም።

በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት የሰላም ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ  ነፍጥ ካነገቡ ሃይሎች የመጨረሻው ሆኖ ሀገር ቤት ገብቷል።

የግንባሩ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአስመራ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ከአንድ ወር በፊት ኦብነግ የ40 ዓመቱን የብረት ትግል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃኝ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ያመራበት ታሪካዊ ጉዞ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ተጨማሪ ነጥብ የሚያስቆጥር ሆኗል።

የኦብነግ አመራሮች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ በተለይም በጂጂጋ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የሶማሌ ክልል መንግስትም ኦብነግ ሰላማዊ ትግሉን በመቀላቀሉ ለሶማሌ ክልል ነዋሪዎች የስቃይ ዘመን ተዘግቷል ሲል የደስታ መግለጫ አውጥቷል።

ኦብነግ ለሰላማዊ ትግል እያሟማቀ መሆኑን በመግለጽ ሰሞኑን የግንባሩ ዋና ጸሀፊ አቶ አብዱራህማን ሼህ መሃዲ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አብዱራህማን እንዳሉት የኢትዮጵያን ህገ መንግስትና የተባበሩት መንግስታትን መርሆችን በማክበር በምርጫ በሰላማዊ መንገድ ተፎካካሪ ፖርቲ ለመሆን ተዘጋጅተዋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የግንባሩ የውጭ ጉዳይ ሀላፊና ቃል አቀባይ አቶ ሀሰን አብዱላሂ በበኩላቸው በምርጫ ቦርድ በፓርቲ ደረጃ ለመመዝገብ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኦብነግ ሰላማዊ ትግሉን የሚቀላቀልበትን ምዕራፍ በይፋ ይከፍታል ብለዋል።

ምርጫውን ለማካሄድ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ልታገኝ ይገባል ያሉት አቶ ሀሰን በኢትዮጵያ አሁን ባለው ችግር ምርጫ ማካሄድ ተገቢ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ቀውሱ በአስቸኳይ ረግቦ ምርጫ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ግን በፓርቲ ደረጃ ተመዝግበው በክልልና በሃገር አቀፍ ምርጫ በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አቶ ሀሰን ገልጸዋል።

ምርጫ የሚኖረው ህዝብ በሰላም መምረጥ የሚችልበት እድልና ሁኔታ ሲመቻች ነው ያሉት አቶ ሀሰን አሁን ባለው ቀውስ ከቀጠለ የምርጫው ጊዜ ቢራዘም ኦብነግ ተቃውሞ እንደማይኖረው ገልጸዋል።

አቶ ሀሰን እንደሚሉት የተፈጠረውን መልካም የለውጥ ጅምር ለማገዝ ኦብነግ ከመንግስት ጎን ይቆማል።

በየቦታው እሳት የሚለኩሱትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በኦብነግ ስም ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።