ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አመራር አሁንም እንዳልተረጋጋ እየተነገረ ሲሆን፤ የድርጅቱ አመራር አባላት በመስከረም አጋማሽ ተጀምሮ ያልተቋጨውን ስበስባ ለመቀጠል አዳማ መክተታቸው ታውቋል።
ከኢትዮጵያ የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፤ ከወረዳ ጀምሮ የሚገኙት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላትም በዚህ ስበሰባ እንደተካከቱ ለማወቅ ተችሏል።
ቀደም ሲል በአቶ አባዱላ ገመዳ፤ ኩማ ደመቅሳና ጁነዲን ሳዶ ይመሩ የነበሩት ሶስት አንጃዎች ወደአራት አድገው፤ አንድ አድፋጭ ቡድንም እንደተፈጠረ ታውቋል።
ኦህዴድ ከሁለት ሳምንታት በፊት ባደረገው ግምገማ አቶ ጁነዲን ሳዶን ከስራ አስፈጻሚነትና ከማእከላዊ ም/ቤት አባልነት አንስቶ ተራ አባል እንዳደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ በጠቅላይ ሚንስተር አሿሿም ላይ፤ ኦህዴድ በማእከላዊ መንግስት ባለው ስልጣንና በሙስና ምክንያት በአመራሩ መካከል የተነሳው ከፍተኛ ሽኩቻ እንደተካረረ ታውቋል።
ጠ/ሚንስትርነቱንና ምክትል ጠ/ሚነቱን ደኢህዴንና ብአዴን ከተቀራመቱት በኋላ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱ ለኦህዴድ እንዲሰጥ አባላት ግፊት ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ከጠ/ሚሩ ቢሮ በወጣ ደብዳቤ አቶ ብረሀነ ገ/ክርስሮስ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ተደርገው መሾማቸው ይታወቃል።
የተፈጠረው ክፍፍል ሳይቋጭ ወደ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መክፈቻ ስብሰባ ያመራው ከፍተኛ አመራርና ሌሎች የድርጅቱ አመራር አባላት በትናንትናው እለት ለአስቸኳይ ስብሰባ ወደ አዳማ ማምራታቸው ታውቋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የኦሮምኛው ክ/ጊዜ አንድ የኦህአዴድ ማእከላዊ ም/ቤት አመራር በመካከላቸው የተፈጠረውን ጭቅጭቅ “ተባላን” በሚል ቃል የእንደገለጹት የሚታወስ ሲሆን፤ እኚሁ ሰው በኦህዴድ አካሄድ ላይ የሕወሀትን ጣልቃገብነት ማንሳታቸውም ይታወሳል።