(ኢሳት ዜና–መስከረም 4/2010)ኦህዴድና ሶህዴፓ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው።
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን ከተከሰተውና ተባብሶ ከቀጠለው እልቂት ጋር ተያይዞ የሁለቱ ክልላዊ መንግስታት ቃል አቀባይ ቢሮዎች አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ የሚያደርግበት መግለጫ አውጥተዋል።
በአቶ አብዲ መሀመድ ኦማር የሚመራው የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ ሰሞኑን በኦሮሚያና ሶማሌ ወሰን አካባቢ የተነሳው ግጭት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሚደገፍና በክልሉ የታጠቁ ሃይሎች፣በክልሉ ፖሊስ፣ሚሊሺያና የኦነግ ቄሮ አባላት የተቀነባበረ እንደሆነ ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ደግሞ በግልጽ የኦነግ አባልነቱን በተግባር ያረጋገጠ በማለት ከሶታል።
ሰሞኑን በአወዳይ ከተማ ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂና እስከዛሬ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተገድለዋል ብሏል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የጀመረውን የዘረኝነት ጭፍጨፋ አጠናክሮ መቀጠሉን ያመላክታል በማለት በመግለጫው ዘርዝሯል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የጸጥታ ሃይሉ በክልሉ ላይ ከ20 አመት በላይ የኖሩ ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በደም የተዛመዱ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የወሰደው ርምጃ የሱማሌ ክልል ህዝብና መንግስትን በእጅጉ አስቆጥቷል ብሏል።
ጉዳት አድራሾቹ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር አጥብቆ እንደሚሰራ አሳስቧል።
በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለአጸፋ ምላሽ ባወጣው መግለጫ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪና ሃላፊነት የጎደለው ነው ብሎታል።
የተጣለበትን ሕዝባዊና መንግስታዊ ሃልፊነት ከመሸሽም አንጻር ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በማለት ፈርጆታል።
መግለጫው የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ልዩ ሃይል አደራጅቶ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረሱና ሰላማዊ ዜጎች ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መደረጉ ከፌደራሊዝሙ በተቃራኒ መቆሙን ያመላክታል ብሏል።
የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የለማ መገርሳን አስተዳደር በአሸባሪነትና በኦነግነት ፈርጆ ያወጣው መግለጫ ሀላፊነት በጎደለው አግባብ የተጻፈና ወንጀልም ጭምር በመሆኑ ህገመንግስቱን ተከትለን በህጋዊና በአስተዳደራዊ መንገድ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልጻለን በማለት ያስጠነቅቃል።
መግለጫው ከዚህ በፊት የኦሮሞ ተወላጆችንና የክልሉን አመራሮች በኦነግነት መፈረጅና ለማሸማቀቅ መሞከር ከበርካታ አመታት በፊት ሲደረግ የነበረ አሁን ጊዜው ያለፈበት ተራ ፍረጃ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን በማለት ያስገነዝባል።
መግለጫው ከዚህ በፊት የኦሮሞ ተወላጆችን በኦነግነት የሚፈርጀው አካል ማን እንደሆነ የገለጸው ነገር የለም።
በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ግጭቱን ከጀርባ ሆኖ በማቀነባበር የሚወቀሰው ይህወሃት ቡድንም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ፍጅቱን ለማስቆም ዳተኛ ሆነው ተገኝተዋል።